በመተከል ዞን የተፈጠረው ችግር የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ያለመ ነው – አቶ ተስፋዬ በልጅጌ

2014

ታህሳስ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተፈጠረው ችግር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን የማስተጓጎል ዓላማ ያለው መሆኑን በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የፖለቲካና ሕዝባዊ ውይይቶች መሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ “የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች ጥረት ቢኖርም ምኞች እንጂ በተግባር የሚሞከር አይደለም” ብለዋል።

በመተከል ዞን በከሰረው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን የማዳከም ተልዕኮ የተሰጣቸው እኩይ ቡድኖች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውሰው፤ የጥቃቱ ዋነኛ ዓላማ የግድቡን ግንባታ ማጓተትና ከተቻለም ማስቆም መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው አሰቃቂ ጥቃት የሚፈጸመው ዜጎች በመንግስት ተስፋ ቆርጠው ወደለየለት የእርስ በእርስ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል።

የዚህ እኩይ ተግባር ፈፃሚዎች የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች እንደሆኑ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ዘመናትን በተሻገረ ቁጭት በራሳቸው ሃብት የሚገነቡትን የሕዳሴ ግድብ ለማስተጓጎል መሞከር ከምኞት እንደማያልፍ አረጋግጠዋል።

የግድቡ ግንባታ በተሻለ ፍጥነት እየተከናወነ ስለመሆኑም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

በመተከል ዞን በተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል የሕግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በአካባቢው ስጋት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ላይ ጠንካራ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።በሕግ ማስከበር እርምጃው በርካታ ታጣቂ ሃይሎች እጃቸውን እየሰጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።