የትራንስፖርት ችግር በዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴችን ላይ ጫና አሳድሯል -- የመዲናዋ ነዋሪዎች

135

ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) የትራንስፖርት ችግር በዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ተገልጋዮች ተናገሩ።

የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ የሕዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራሁ ነው ብሏል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተገልጋዮች እንደሚሉት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከተጠቃሚው ጋር ሲነጻጸር በቂ አይደለም።

በዚህ ምክንያት በሚፈለግበት ሠዓት የስራ ገበታ ላይ ለመገኘት እንዲሁም ከስራ መልስ ወደቤት ለመግባት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ ሰዎች ከስራ ገበታቸው እንዲስተጓጎሉ ከማድረጉ ባሻገር ለእንግልት እየዳረጋቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ትራንስፖርት ለማግኘት የሚፈጠረው መሽቀዳደምና መጨናነቁ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ለጉዳት እየዳረጋቸው መሆኑም ተመልክቷል።

ሰዎች ታክሲ ሲያጡ በእግራቸው ለመጓዝ እንደሚገደዱና ይህም ለሌባ ዝርፊያ እየዳረጋቸው መሆኑም ተነግሯል።

ተሳፋሪዎች ወደ ትራንስፖርት ሲገቡ በሚፈጠር መጨናነቅ ንብረታቸውን እየተዘረፉ ነውም ተብሏል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ በበኩላቸው በተጠቃሚዎች የሚነሱ ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸውን ተናግረዋል።

የችግሩ ምክንያቶች የትራንስፖርት አቅርቦቱና የተጠቃሚው ፍላጎት አለመመጣጠንና የከተማዋ መንገዶች ዘመናዊ አለመሆን ናቸው ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት የብዙሃን ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከችግሮቹ አንዱ የተጠቃሚውና የትራንስፖርት አቅርቦቱ አለመመጣጠን በመሆኑ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ 850 አውቶቡሶች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶችን በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች በማሰማራት ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ቢሮው ችግሩን ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን አዘጋጅቶ እየሰራ ነው።

ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማቃለልም የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራበት ነው ብለዋል።

የትራንስፖርት ዘርፉን የተሳለጠ በማድረግ የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታት መሰል ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም