በአሶሳ የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

58

አሶሳ፤ታህሳስ 24/ 2013 (ኢዜአ) በአሶሳ ከተማ የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት እስከ አምስት ሺህ ብር ሲሸጡ የነበሩ ሶስት ተጠርጣሪዎችን ዛሬ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

ከሀሰተኛ ማስረጃዎች መካከል የሃገር መከላከያ ሠራዊት መታወቂያ እንደሚገኝበት ተጠቅሷል።

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ምክትል ኢንስፔክተር ደረጄ ኢታና ለኢዜአ እንደገለጹት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሃሰተኛ ማስረጃዎችን ሲያዘጋጁ ተደረሶባቸው ነው፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንደኛው በአሶሳ ከተማ በሞተር ብስክሌት ሲጓዝ ከክልሉ ፖሊስ ጋር የከተማውን ጸጥታ በማስከበር ላይ ያለው የሃገር መከላከያ ሠራዊት በጥርጣሬ አስቁሞ መታወቂያ ሲጠይቀው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ነኝ በሚል ግብግብ መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

ግለሰቡ በክልሉ ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ ቶንጎ ከተማ ነዋሪ እንደሆነ የገለጹት ኢንስፔክተር ደረጄ፤ ወንጀሉን የሚፈጽመው በአሶሳ ከተማ ተቀምጦ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ከፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ አውጥቶ በተጠርጣሪው ቤት ባደረገው ፍተሻ የተለያዩ የሃገር መከላከያ ሠራዊትና የስደተኞች መታወቂያ፣ የጂማ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲፕሎማ ማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ሃሰተኛ መንጃ ፈቃድ፣ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ መታወቂያ፣ የመኖሪያ ቤት ይዞታ መረጋገጫ ካርታ ለተለያዩ ሰዎች ያዘጋጅ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ሃሰተኛ የፌደራል ፖሊስ አባል ማስረጃ እና የስራ ልምድ አስመስሎ በማዘጋጀት ግለሰቦችን መንግስታዊ ባልሆነ ተቋማት ሲያስቀጥርበት የነበረ ሃሰተኛ የሰነድ ማስረጃም መገኘቱንም አመልተዋል፡፡

በሚያዘጋጃቸው ሃሰተኛ ሰነዶች እስከ አምስት ሺህ ብር እንደሚቀበል ፖሊስ በምርመራ ማጣራቱን አስረድተዋል፡፡

ምክትል ኢንስፔክተር ደረጀ ሁለት የዚሁ ግለሰብ አገናኝ እና ደላሎችም ወንጀሉን ለማስፈጸም ከሚጠቀሙት ባጃጅ ታክሲ ጋር አብረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ለጸጥታ ሃይሉ መረጃ በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም