ዜጎች ሰርተው ከራስ ባለፈ ቤተሰብና ሀገርን መጥቀም የሚችሉት ሰላምና ሀገራዊ አንድነት ሲኖር ነው…አቶ ደስታ ሌዳሞ

1749

ሀዋሳ፤ታህሳስ 24/2013(ኢዜአ) ዜጎች ሰርተው ከራስ ባለፈ ቤተሰብና ሀገርን መጥቀም የሚችሉት ሰላምና ሀገራዊ አንድነት ሲኖር ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብሮች በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸው 5 ሺህ 626 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ።

በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ሀገሪቱ ለሁሉም የሚበቃ ሀብት አላት ያሉት ርዕሰ መስስተዳድሩ፤ ጥላቻና መናቆር የተሞላባቸውን እኩይ ድርጊቶች ለማንም የማይበጁ በመሆኑ የተማረው ሀይል ይህን በማስወገድ አንድነትና አብሮነትን በማቀንቀን እጅ ለእጅ ተያይዞ መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል።

“የዛሬ ተመራቂዎች በመንግስት መስሪያ ቤት ለመቀጠር ብቻ ሳይሆን የራሳችሁንም ስራ በመፍጠር ለሌሎች መትረፍ የምትችሉና ለሀገራችሁም የበኩላችሁን ሚና የምትወጡ መሆን አለባችሁ” ሲሉም ርዕስ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ስድስት በሶስተኛ ዲግሪ፣ 514 ሁለተኛና ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸውንና 34 በመቶው ሴቶች እንደሆኑ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ገልጸዋል።

ከስድስት ወራት በፊት መመረቅ የነበረባቸው ተማሪዎች የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ቢያስተጓጉለውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ባደረጋችሁት ተጋድሎ ለምረቃ መብቃታችሁ አስደሳች ነው ብለዋል።

የኮሮና  ቫይረስን በመከላከል የገጽ ለገጽ ትምህርት መቀጠል እንዲቻል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በመስራት  ተማሪዎቹን  ማስመረቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ተመራቂዎች ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ ሀገሪቱን  እየፈተነ ያለውን ዘረኝነት፣ ጥላቻና አድሏዊ አሰራር እንዲሁም ሙስናን በመጠየፍ በወንድማማችነትና አንድነት በጋራ ለሀገር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ዜጎች ሰርተው ከራስ ባለፈ ቤተሰብና ሀገርን መጥቀም የሚችሉት ሰላምና ሀገራዊ አንድነት ሲኖር ነው።

ከተመራቂዎቹ መካከል በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የተከታተለችው ሀዋ የሱፍ በሰጠችው አሰተያየት የኮሮና ቫይረስ ጫና ብቻ ሳይሆን የአራት ወር ልጇን ጭምር በተገቢው መንገድ በጥንቃቄ እያሳደገች ትምህርቷን ተከታትላ ማጠናቀቅ እንደቻለች ገልጻለች።

በስታትስቲክስ የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር በማዕረግ የተመረቀው ወልዱ ዮሐንስ በበኩሉ ከኮሮና በመጠንቀቅ ትምህርቱን ማጠናቀቁን ገልጾ ቀጣይ ገቢ ተማሪዎችም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግሯል።

ኮሮና ብቻ ሳይሆን ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን በመረዳት ለሠላማዊ የትምህርት ላይ ቆይታ ተማሪዎች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁሟል።