ከጭቆና የወጣው የትግራይ ሕዝብ የተስፋ ብርሃን እያየ ነው … የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

1828

መቀሌ፤ታህሳስ 24/2013(ኢዜአ) በሕግ ማስከበር እርምጃው ከጭቆና የወጣው የትግራይ ሕዝብ የተስፋ ብርሃን እያየ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

የትግራይ ሕዝብ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን ሊቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

የህወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።

አገር በሚጠብቅ ሠራዊት ላይ በገዛ ወገኑ እንደዚህ አይነት ጥቃት መፈጸሙ ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችልና ይደረጋል ተብሎ የማይጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የደረሰው ጥቃት የትግራይን ሕዝብ የማይመጥን ባሕሉንም የማይወክል ነው ብለዋል።

መንግስት የወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ትክክለኛና ተገቢ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ እርምጃው ሕዝቡን ያስደሰተ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሕግ ማስከበር እርምጃው የትግራይ ሕዝብ የብርሃን ጭላንጭል ማየት እንደጀመረና ተስፋ መሰነቁንም ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በመቀሌ ከተማ የወሰደው እርምጃ ጥንቃቄ የተሞላበት በመሆኑ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን የገለጹት ነዋሪዎቹ ከተማዋ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኑን አክለዋል።

የሕወሓት አመራሮች ተመልሰን እንመጣለን እያሉ የሚነዙትን ፕሮፖጋንዳ ሕዝቡ እንደማይቀበለውና ቦታ የማይሰጠው መሆኑንም ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን ነጻነትና ሠላም ሊያጣጥመው ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ አሁን የሚያስፈልገው ልማትና ስራ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ሕዝቡ በትግራይ ክልል ከተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በጋራ መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ አጠናቆ ወደ “ወንጀለኞችን ማደንና መልሶ ማቋቋም” ምዕራፍ መሸጋገሩ ይታወቃል።

በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከትግራይ ክልል የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያየ ነው።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ መሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀመሩ እየሰራ ሲሆን በክልሉ የሚገኙ ሕዝባዊ ተቋማትም አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

በተያዘው ሣምንት በመቀሌ ከተማ የባንክ አገልግሎት መጀመሩ የሚታወስ ነው።