የኮሮናቫይረስ ክትባት ማስገባት የሚያስችሉ ዝግጅቶች ሲጠናቀቁ ክትባቱን መስጠት ይጀመራል ... ጤና ሚኒስቴር

84

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ክትባት ማስገባት የሚያስችሉ የላቦራቶሪና ሌሎች ዝግጅቶችን ስታጠናቅቅ 20 በመቶ ዜጎቿ ላይ ክትባቱን እንደምትጀምር የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ። 

ክትባቱ መስጠት ሲጀመር ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችና ዳር ድንበር የሚጠብቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ያገኛሉ ብለዋል።

የተለያዩ አገራት እስካሁን ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን እያፈላለጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ክትባትን እንደ አንድ መፍትሔ በመውሰድ ለሕዝቦቻቸው ተደራሽ እያደረጉ ነው።

እንደ ወይዘሮ ሳህረላ ገለጻ ኢትዮጵያም ሳይንሳዊ ሁኔታዎችን ተከትላ ክትባቱን ለማስገባት ስትዘጋጅ መቆየቷን ገልፀዋል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግም ክትባቱን መፈተሻ ላቦራቶሪ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እየተገጣጠመ ይገኛል ብለዋል።

ክትባቱ ወደ አገር ቤት ከመግባቱ በፊት የላቦራቶሪ ፍተሻዎችን ሲያልፍ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ይደረጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት ለሚመራው የክትባት ድጋፍ ሰጪ ተቋም "ኮቫክስ" የቦርድ አባል መሆኗን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ዜጎችን መከተብ የሚያስችል ድጋፍና ግብዓቶችን ለማግኘት እንደሚረዳት ተናግረዋል።

አገሪቷ ለማስገባት ካሰበችው ከጠቅላላው 20 በመቶው ክትባት በግዥና ከለጋሾች ለማሟላት ታሳቢ መደረጉን ገልጸው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ እጥረትን ለመፍታት ቃል የገቡ አገራት መኖራቸውን አክለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ክትባቱን እንደ አገር ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነም ተናግረው፤ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ እንደ ሕክምና ባለሙያዎችና ዳር ድንበር የሚጠብቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል።

ድጋፉ ከለጋሽ ድርጅቶች ሲጘኝ ለሁሉም ዜጎች በተለያየ ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም