የአምራቾችን ችግሮች ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24/2013(ኢዜአ) አምራቾች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የዘርፉ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ገለጸ። 

ባለሥልጣኑ የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድሎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ ከባድርሻ አካላት ጋር ትናንት ተወያይቷል።

ለውይይት መነሻ በባለሥልጣኑ የቀረበው የዳሰሳ ጥናት እንዳመላከተው፤ በአነስተኛና መካካለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች በርካታ ችግሮች እያጋጠሟቸው ነው።

ከእነዚህም መካከል የጥሬ ዕቃ አቅርቦት የተነሳ ሲሆን የጥሬ እቃ መወደድ፣ ገበያ ላይ አለመኖርና የውጭ ምንዛሬ አለማግኘት ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው ተጠቅሷል።  

የመሥሪያ ቦታ አለመመቸት፣ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረትና የገበያና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እጥረቶች ዘርፉን በተደጋጋሚ ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል ናቸው ተብሏል።

ያም ሆኖ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትም ለኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ተብሎ የሚሰጣቸውን የመሥሪያ ቦታና ብድር ለሌላ ዓላማ እያዋሉት መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል።  

በውይይቱ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላትም እነዚህ ችግሮች የዘርፉ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው መሆናቸውን ጠቁመው ሁነኛ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

ጎን ለጎንም በዘርፉ ያሉ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩና ከብድር አሰጣጥ ሥርዓትና ከተርን ኦቨር ታክስ ጋር የሚነሱ የንግድ ሥርዓት ሂደቶች በድጋሚ ሊጤኑ እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።

የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ባለሥልጣኑ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ርብርብ ያደርጋል ብለዋል።

ለዚህም በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸውና ለዚህም ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በተጓዳኝ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለዘርፉ የሚመጥን የሠው ሃይል በማፍራት ረገድ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው ይህም ትኩረት የሚሹ ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል።

በሌላ በኩል በተለይም ሼዶች ሲተላለፉና ብድር ሲሰጥ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በቅጡ ማጤንና ትክክለኛ ውሳኔ በመወሰን ለዘርፉ እድገት ሃላፊነትን መወጣት ይገባል ብለዋል።

ሸማቹ ኅብረተሰብም የአገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ዘርፉን እንዲደግፍ ጠይቀው አምራቾችም በአገር ውስጥ ያሉትን ሃብቶች መለየት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም