በመተከል ለተፈጠረው ችግር እጃቸው ያለበት የዞኑ አመራሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ የዞኑ የመንግስት ሰራተኞች ጠየቁ

77

ታህሳስ 24 /2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ ለተፈጠረው ችግር የህወሃት ጁንታ ተላላኪ በመሆን እጃቸው ያለበት የዞኑ አመራሮች በህግ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው የዞኑ የመንግስት ሰራተኞች ተናገሩ።

በመተከል ዞን በሁሉም ወረዳዎች የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በግልገል በለስ ከተማ ውይይት አድርገዋል።

ሰራተኞቹ በዜጎች ላይ የተፈፀመውን በጭካኔ የተሞላ ግድያ፣ ዘረፋና የንብረት ማውደም ተግባር በፅጽኑ አውግዘዋል።

ድርጊቱ በፅንፈኛ ታጣቂዎችና በዞኑ ባሉ የህወሃት ጁንታ ተላላኪ አመራሮች ደጋፊነትና አቀናባሪነት የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዞኑ ህዝብ በድርጊቱ ማዘኑን ገልጸዋል።

ለጥቃቱ መፈፀም የህወሃት ተላላኪ አመራሮችና ከመንግስት ሰራተኞችም መካከል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉ እንዳሉ ጠቁመዋል።

"እንደ አጠቃላይ በመተከል ዞን ለተፈጠረው ችግር ለጥፋት የሚሰሩ የአመራር አባላት ተሳትፎና ትብብር አለበት" ሲሉም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የአገር መከላከያ ሰራዊት በጁንታው ላይ የወሰደውን እርምጃ ለመደገፍ የወጡ ዜጎችን ሲቃወሙ የነበሩ የልዩ ሃይል አባላትና አመራሮች እንደነበሩም አስተያየት ሰጭዎቹ አንስተዋለ።

"በዞኑ አመራሩ ለህዝቡ ተጠቃሚነት በትኩረት እየሰራ ባለመሆኑ በርካታ የጉሙዝ እናቶች አሁንም ጫካ ውስጥ ይወልዳሉ" ብለዋል የመንግስት ሰራተኞቹ።

ወጣቶች ለጥፋት ቡድኑ በህወሃት እየተመለመሉ አልማሀል ወደሚባል ቦታ ሲወሰዱ የጉሙዝ እናቶች "ልጆቻችን እየተወሰዱ ነው" የሚል ጥያቄ ሲያነሱ የሰማቸው አመራርም እንዳልነበር አስታውሰዋል።

"ወጣቶችን እየመለመሉ በጥቆማ የተያዙትም የጥፋት ተላላኪዎች ውዲያውኑ ይለቀቁ ነበር" ብለዋል።

በክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ጌታነህ ሰዲ በመተከል ዞን ከመንግስት ሰራተኞቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም በዞኑ የተፈጠረው ችግር የጉሙዝን ማህበረሰብ የማይወክል የጥፋት አላማ ባላቸው አካላት የተቀነባበረ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም ህዝቡ ጥፋተኞችን በማጋለጥ ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም በጋራ መስራቱን እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም