በወላይታ ዞን ለ''ገበታ ለሀገር'' ፕሮጀክት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

67

ሶዶ ታህሳስ 24/2012 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ የሚውል ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በቀጣይም ለፕሮጀክቱ ድጋፍ ሀብት የማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

የአስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ አቶ ተመስገን ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዞኑ ማህበረሰብ በፕሮጀክቱ ዙሪያ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል  እየተሰራ ነው።

እስካሁን በተደረገው ጥረት በዞኑ የሚገኘው የመንግስት ሠራተኛ በፍላጎቱ አቅሙ የፈቀደውን ያህል እና አመራሩም የአንድ ወር ደመወዝ በማዋጣት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል።

በሀገር ደረጃ ከሚገነቡት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሚገኝበት ሥፍራ ለዞኑ አዋሳኝ መሆኑ የጠቆሙት አቶ ተመስገን ፤ ባለሀብቱና የንግድ ማህበረሰብም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የሶዶ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ጸጋዬ በበኩላቸው፤ ለፕሮጀክቱ መሳካት እንዲያግዝ የአንድ ወር ደመውዛቸው መስጠታቸው ጠቅሰው  ፕሮጀክቱ ለሀገርና ህብረተሰቡ ካለው ጠቀሜታ አንፃር ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሶዶ ከተማ ነዋሪ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ በፕሮጀክቱ ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ እንደሚዘጋጅም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም