በአዳማ ከተማ ዘመናዊ የግብርና የፈጠራ ውጤቶች ባዛር ተከፈተ

67

አዳማ፣ ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) ዘመናዊ የሆኑ የተለያዩ የግብርና ፈጠራ ውጤቶችን ያካተተ ባዛር ዛሬ በአዳማ ከተማ ተከፈተ።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባዛሩን ከፍተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በወቅት እንደገለጹት፤ በባዛሩ የታደሙት የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችና የምርምር ውጤቶች ለቀጣይ የግብርና እድገት ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።

በተለይ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች የመውቂያ፣ የእርሻና የማጨጃ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም የምርጥ ዘር የምርምር ውጤቶች የግብርና ስራውን ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በትክክል የሚደግፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የፈጠራ ውጤቶች ለአርሶ አደሩና ተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በተለይ የሞዴል አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ተሞክሮ ለሁሉም አምራች እንዲደርስ የምርምር ማዕከላት እና የዘርፉ ሙያተኞች በቅንጅት መስራት አለባቸው" ብለዋል።

በባዛሩ ከሞዴል አርሶ አደሮች፣ ከ80 በላይ የምርምር ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ድርጅቶች፣ የምርጥ ዘር ማባዣ ማዕከላት እየተሳተፉ ነው።

የክልሉ ሞዴል አርሶ አደሮች፣ ምርምር ተቋማትና የግብርና ሜካናይዜሽን የፈጠራ ውጤቶቻቸውን አቅርበዋል።

ነገ  ደግሞ ከ600 በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች፣ የምርምር ተቋማት፣ ሙያተኞች እውቅና እንደሚሰጥ ከወጣው መርሀ ግብር ማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም