ኢትዮጵያ እንደገና ጥምቀትን በጎንደር" በሚል በዓሉን ለማክበር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው - የጎንደር ከተማ አስተዳደር

194

ታህሳስ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) የጥምቀትን በዓል "ኢትዮጵያ እንደገና ጥምቀትን በጎንደር" በሚል መሪ ሃሳብ በልዩ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በዓሉ የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና የጎረቤት አገራትን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የበለጠ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ጥምቀት በኢትዮጵያ በተለይም በጎንደር ሃይማኖታዊ ይዘቱን ሳይለቅ በየዓመቱ ይከበራል። 

የከተማዋ የባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል "ኢትዮጵያ እንደገና ጥምቀትን በጎንደር" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

"የከተማዋን ቱሪዝም ለማነቃቃት ሲባል በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በዓሉን በድምቀት ለማክበር ታቅዷል" ብለዋል።

በበዓሉ የተለያዩ ስነ-ስርዓቶች እንደሚከናወኑና በርካታ እንግዶችም እንደሚታደሙ ገልጸዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የሕዝብ መገፋፋትና መጨናነቅን ለማቃለል ሰፋፊ የብረት መድረክ፣ በቂ የፀበል መርጫ እንዲሁም የበዓሉን አከባበር የሚያሳይ ትልቅ ስክሪን መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ሆቴሎችና የባሕል ምሽት ቤቶች ለበዓሉ ታዳሚያን በቂ መስተንግዶ እንዲሰጡና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንም አቶ አደባባይ ተናግረዋል።

በበዓሉ ላይ የኤርትራና የሱዳን ሕዝቦች ተወካዮች እንደሚታደሙም ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው "የዘንድሮው የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያዊያንና የጎረቤት አገራት ሕዝቦችን ትስስር ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል" ብለዋል።

በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ከፀጥታ ተቋማት፣ ከወጣቶች፣ ከባለሃብቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ከንቲባው ቱሪስቶችና እንግዶች ያለምንም ስጋት ወደ ጎንደር በመምጣት በልዩ ሁኔታ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል እንዲታደሙም ጥሪ አቅርበዋል።

የጥምቀት በዓል ሣምንት ተብሎ በተሰየመው ከጥር 1 እስከ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የባህል ትውውቅ፣ የቁንጅና ውድድር፣ የአጼ ቴዎድሮስ የልደት በዓል፣ ባዛር፣ የሙዚቃ ድግሶችና ሌሎች ሁነቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

ከአገር ውስጥና ከውጭ አገሮች በዓሉን ለመታደም ከሚመጡ ባለሃብቶች ጋር የኢንቨስትመንት ፎረም እንደሚካሄድ አቶ ሞላ ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በዓሉን ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች የተለመደውን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕሉን በተግባር እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል። 

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የባሕል፣ የሳይንስና የትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም መመዝገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም