በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚጓጓዘው የመጀመሪያው የጭነት እቃ ኢትዮጵያ ገባ

123

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚጓጓዘው የመጀመሪያው የጭነት እቃ ኢትዮጵያ ደርሷል።

የዲ.ኤች.ኤልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሽርክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ኩባንያ ከአፍሪካ የኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የጭነት እቃ ማስተናገጃ ተርሚናል በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የጭነት አገልግሎትን ዛሬ በጋራ አስጀምረዋል።

በጭነት አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ የኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ የበላይ ጠባቂ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ የስራ ክፍል የማህበረሰብ መረጃ ንዑስ ዘርፍ ሃላፊ ሞክታር የድላይና ጥሪ የደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ወደ ስራ በገባበት ዕለት የጭነት አገልግሎት መጀመሩ የዛሬውን ቀን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በንግድ ቀጠናው የታሸጉ እቃዎችና የተለያዩ ምርቶችን እንደሚያጓጉዝም ተናግረዋል።

በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ የካርጎ ጭነት ስለሚያጓጉዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የጭነት አገልግሎት መልካም የገበያ ዕድል እንደሚፈጥርለት አመልክተዋል።

አየር መንገዱ በአፍሪካ አገራት ጭነቱን በማጓጓዝ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል።

የአየር መንገዱ የካርጎና ሎጂስቲክ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አባዲ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚጓጓዘው የመጀመሪያው የጭነት እቃ ከአፍሪካዊቷ አገር እስዋቲኒ በአየር መንገዱ አማካኝነት ተጓጉዞ ትናንት ኢትዮጵያ መድረሱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የጭነት ዕቃውን ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ግብጽና ኒጀር እንደሚያጓጉዝም ተናግረዋል።

በቀጣይ በሌሎች አገራት የታሸጉ እቃዎችን ወደ ሌሎች አገራት እንደሚያጓጉዝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕና የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክ አገልግሎት ዲ.ኤች.ኤል እ.አ.አ በ2018 በተፈራረሙት ስምምነት የዲ.ኤች.ኤልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሽርክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ኩባንያ በዚያው ዓመት ማቋቋማቸውን አስታውሰዋል።

በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የጭነት አገልግሎት የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትና ሽያጭ ስራ እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ የኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ የበላይ ጠባቂ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጭነት አገልግሎቱ በአፍሪካ 2063 አጀንዳ ማዕቀፍ የምንፈልጋትን አፍሪካ መፍጠር ለሚለው ራዕይ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ለማሳካት አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።

የጭነት አገልግሎቱ መጀመር የአፍሪካ አገራትን የእርስ በእርስ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት አገራት ለነጻ የንግድ ቀጠናው ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአፍሪካ የኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ ሶኮኩ /በስዋህሊኛ የጋራ ገበያ/ በሚል ስያሜ ያዘጋጀው የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ዘዴ ዛሬ በይፋ መጀመሩንም አብስረዋል።

ግብይት ዘዴው የአፍሪካ አገራት ያላቸውን የንግድ ልውውጥ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ያለው ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው የጭነት አገልግሎቱና በአጠቃላይ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን ተጠቃሚነት የሚጨምር መሆኑን ገልጸዋል።

ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩና ለሚያስገቡ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርና ለስራ ዕድል ፈጠራ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የዚህ የጭነት አገልግሎት ሰጪ መሆኑም የአፍሪካ ኩራት መሆኑን ዳግም ያስመሰከረበት ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ የስራ ክፍል የማኅበረሰብ መረጃ ንዑስ ዘርፍ ሃላፊ ሞክታር የድላይ የጭነት አገልግሎቱ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ወደ ስራ በገባበት ቀን መጀመሩ ለአፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የመጀመሪያው ጭነት የሚያጓጉዝ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት ነጻ የንግድ ቀጠናው የሚፈጥራቸውን የንግድ ዕድሎችና አማራጮች በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እውን መሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአፍሪካ ኅብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ የስራ ክፍል የማኅበረሰብ መረጃ ንዑስ ዘርፍ ሃላፊ ሞክታር የድላይ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን ሽልማት አቶ ተወልደ ገብረማርያም ተቀብለዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት እ.አ.አ በ2018 በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ልዩ ስብሰባ ከኤርትራ በቀር 54 የአፍሪካ አገራት ፈርመዋል።

ስምምነቱን ወደ ስራ ለማስገባት 22 አገራት በአገራቸው ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ማስፀደቅ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 31 አገራት በማጽደቃቸው ስምምነቱ ዛሬ ወደ ስራ ሊገባ አስችሎታል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በያዛቸው አገራት ብዛት በዓለም ትልቁ የንግድ ቀጠና የሚያደርገው ሲሆን 54ቱ አገራት አሁን ያላቸው አጠቃላይ የምርት መጠን 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ነጻ የንግድ ቀጠናው የአፍሪካ አገራትን የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ከማሳደግ ባለፈ የኤክስፖርት አቅማቸውን በማጎልበት ለኢኮኖሚ እድገታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም