የንግድ ሕግ አዋጁ በአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ልክ እየተሻሻለ ነው - ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) ከ60 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የንግድ ሕግ አዋጅ የአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት የደረሰበትን ደረጃ በሚመጥንና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ባማከለ መልኩ እየተሻሻለ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቅ የንግድ ሕግ አዋጁ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ የቀደመው የንግድ አዋጅ የአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት የደረሰበትን ደረጃ በሚመጥንና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሰረት በማድረግ እንደሚሻሻል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።

የንግድ ሕጉን ዘመናዊ ማድረግ ከዚህ በፊት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የቀደመው የንግድ አዋጅ በ1952 ዓ.ም የወጣና አምስት መጽሃፎችን በአንድ ላይ በመያዝ ከፈረንሳይ አገር በመጡ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ነበር።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከወቅቱ ጋር የማይሄዱ አንቀጾች ተቀንሰውና ሁለት አዳዲስ መጽሃፎች ተጨምረውበት በሰባት የመጽሃፍ መድብል የሚጠቃለል የሕግ አዋጅ እንደሚሆን ተገልጿል።

የሚወጡት አዋጆችም ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ በማሰብ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሰረት አባተ ተናግረዋል።

እስካሁን የተሰበሰበው ግብዓት አዋጁን ለማበልፀግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና ከ20 እስከ 30 ዓመታት እንዲያገለግል ታስቦ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ለአብነትም በማሻሻያው ውስጥ ሳይካተት የቀረውና በተገኘው ግብዓት የዳበረው የአክሲዮን ባለድርሻ ያልሆኑ ሰዎች በቦርድ ውስጥ እንዲካተቱ ፈቃድ የሰጠውን ክፍል ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ሰዎቹ የአክሲዮን ባለድርሻ ባይሆኑም ያላቸውን ልምድና እውቀት በመጠቀም የተቀላቀሉትን ድርጅት ለማሳደግ ይችላሉ ተብሏል።

በአክሲዮኖች ውስጥ አነስተኛ ድርሻ ያላቸው ባለሀብቶች ላይ የሚደረሰውን የምዝበራ፣ መረጃ የማጣትና የውሳኔ ሰጪነት ችግር የሚያስቀር መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች በስብሰባዎች ላይ እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ አሰራርም ተካቶበታል።

ድርጅቶች ኪሳራ ውስጥ ሲገቡ እንዴት ማገገም ይችላሉ፣ የውጭ ባለሃብቶች በምን መልኩ በአገር ውስጥ ንግዶች ላይ ይሳተፋሉ የሚሉና ሌሎች አንቀጾች በማሻሻያው መካተታቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም