አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴው እንዲጠናከርና ልማቱ እንዲፋጠን የድርሻችንን እንወጣለን ...የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች

59
መቱ/ ሶዶ ሀምሌ 14/2010 በአገሪቱ እየታየ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አገራዊ ልማቱ እንዲፋጠን በቀሰሙት ሙያ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሙያ መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 933 ተማሪዎች ዛሬ  አስመርቋል። የወላይታ ሶደ ግብርና ቴክኖሎጂ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ለ15ኛ ዙር በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸው ተማሪዎችም ዛሬ ተመርቀዋል። አስተያየታችን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂዎች እንዳሉት በተቋም ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም አገርና ህዝብ የሚጠቅም ስራ ለማከናወን ተዘጋጅተዋል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለውን አገራዊ ለወጥ ለማስቀጠልና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉትን ውጤቶች ለማስቀጠል በትጋት እንደሚሰሩ ነው የገለጹት፡፡ ከመቱ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ የተመረቀው ተማሪ ስረና ማሞ እንዳለው በአሁኑ ወቅት በዶክተር አብይ አህመድ መሪነት እየተመዘገበ ያለው ለውጥ አገሪቱን ወደተረጋጋ ሁኔታ እያመጣ በመሆኑ ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል ፡፡ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ለውጥ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመቀነስ የአገሪቱ እድገት እንዲፋጠን የሚያደርግ በመሆኑ በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማራ በዩኒቨርሲቲው የቀሰመውን እውቀት ተጠቅሞ አገራዊ ልማቱ ለመፋጠን እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የተረጋጋ ሰላምና የለውጥ ጅማሮ በሙያው በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባባት እንዳነሳሳው የተናገረው ደግሞ በምህንድስና የትምህርት መስክ የተመረቀው ገመቺስ በየነ ነው፡፡ “የቀሰምኩትን ሙያና ክህሎት በየጊዜው በማሳደግ አገሪቱ ከእኔ የምትፈልገውን ሁሉ ለማበርከትና ለውጡን ለማስቀጠል ጉጉት አድሮብኛል” ብሏል፡፡ የመቱ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታቸው ሹንኪ በበኩላቸው በዕለቱ ለምረቃ ከበቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች መካከል 1 ሺህ 819 የሚሆኑት በመደበኛው የትምሀርት መርሀ ግብር የተማሩ ናቸው። ቀሪዎቹ 84 ሰልጣኞች በርቀት የትምህርት መርሃ ግበር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመጀመሪያ ዲግሪ በተጨማሪ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 30 ተማሪዎችን በአካውንቲንግና ማኔጅመንት ትምህርት በሁለተኛ ድግሪ ማስመረቁንም ዶክተር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለጻ፣ ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 797 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡   በምረቃ ስነስርአቱ ላይ በውጤታቸው ብልጫ ያመጡ ተማሪዎች ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ የተዘጋጀላቸውን የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና የወላይታ ሶደ ግብርና ቴክኖሎጂ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ለ15ኛ ዙር በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። ተመራቂ ተማሪዎችም በኮሌጁ ያገኙትን ዕውቀት ወደተግባር በመቀየር በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው የለውጥ እንቅስቀሴ ለመደገፍ መዘጋጀታቸው ነው የገለጹት። በዕጽዋት ሳይንስ የተመረቀችው ተማሪ በቴልሄም ብዙነህ "በቀጣይ በንድፈ ሃሳብና በተግባር ልምምድ የቀሰምኩትን ዕውቀት በማካፈል አገሪቱ ለጀመረችው የመደመር መርህ ተፈጻሚነት የራሴን አሻራ ለማሳረፍ ዝግጁ ነኝ " ብላለች። ከእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍልና ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች ብልጫ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫና የሰርተፍኬት ተሸላሚ የሆነው ተማሪ አዲሱ ጋሎቦርሻ በበኩሉ በውጤቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በቀሰመው ዕውቀት ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑንና በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የለውጥ መንፈስ አካል ለመሆን ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግሯል። የኮሌጁ ዲን አቶ መርሁን ፍቅሬ በበኩላቸው እንዳሉት ኮሌጁ በ15ኛው ዙር ያስመረቃቸው 1 ሺህ 304 ሰልጣኞች በደረጃ 4 በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው። ከተመራቂዎች መካከል 457ቱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመው ተመራቂዎች በኮሌጅ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም ተግባር እንዲያውሉት አሳስበዋል። የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ምክትል ኃላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ በኩላቸው የግብርናውን ዕድገት መሰረት ባለው መልኩ ለማስቀጠል ዘርፉን የሚመጥኑና በአግባቡ መምራት የሚችሉ ምሁራንና ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል። ተመራቂ ተማሪዎችም ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ የአገልጋይነት መንፈስን ተላብሰው አርሶና አርብቶ አደሩን በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም