በደብረ ማርቆስ ከተማ በተከሰተውየእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

94

ደብረ ማርቆስ፣  ታህሳስ 23/2013(ኢዜአ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ትናንት ሌሊት በተነሳው የእሳት አደጋ  በ48 የንግድ ሱቆች ላይ ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ አስታወቀ። 

በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተመልክቷል።

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አጃናው አዲስ ለኢዜአ እንደተናገሩት የእሳት አደጋው የደረሰው  ቀበሌ አምስት በሚገኘው የጉልት ገበያ አዳራሽ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ነው።

በዚህም በንግድ ሱቆቹ ውስጥ የነበረ አልባሳት፣ ሸቀጣሸቀጥ፣ቅመማቅመም፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልጸዋል።

የአደጋው መንስኤና የወደመው ንብረት ግምት  በፖሊስ እየተጣራ እንደሚገኝ  የጠቆሙት ዋና ኢንስፔክተሩ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አመልክተዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገው ተሳትፎ የእሳት አደጋው  ወደ ሌሎች ሱቆች ሳይዛመት መቆጣጠር እንደተቻለም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ለእሳት አደጋው መንስኤ የሚሆኑ ተቀጣጣይ ነገሮችን ቀድሞ በማራቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም