በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 10 ሚሊዮን ዶላር በቁጥጥር ስር ዋለ

136
አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2010 በተለያዩ መንገዶች 10 ሚሊዮን ዶላር በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ለማውጣት ሲሞከር በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ህብረተሰቡን ባሳተፈና በተጠና መልኩ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ በተከናወነ ዘመቻ ገንዘቡ ከአገር ሳይወጣ ተይዟል። ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ ይገኛል፡፡ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩን ለመከላከል የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤ በዛሬው ዕለት በሞጆና በአዳማ መካከል በተካሄደ ዘመቻ 570 ሺህ ዶላር መያዙን በአብነት አንስተዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ባለፉት ጥቂት ቀናት በተካሄዱ ዘመቻዎች የጦር መሳሪያ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር ውሏል። ከአንድ ሺህ በላይ የነፍስ-ወከፍ መሳሪያ እና ከ80 ሺህ በላይ ጥይቶች ተይዘዋል። አዲስ አበባ ከተማ ትናንት በተካሄደ ዘመቻ 234 ሽጉጥ ፣ 17 ሺህ ጥይት መያዙንም ነው ኮሚሽነሩ ያመለከቱት። አርማጭሆ 298 ሽጉጥ፣ ሸኖ 53 ሽጉጥ፣ ጋምቤላ 32 ክላሽንኮቭ፣ ሁለት መትረየስ፣ ሰሜን ሸዋ 20 ሽጉጥ እና አንድ መትረየስ መያዙንና ተጠርጣሪዎቹም በቀጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል። የዶላርን ከአገር በህገ-ወጥ መንገድ ማስወጣትና የጦር መሳሪያ ዝውውሩ "ትስስር ሊኖራቸው ይችላል" የሚል ጥርጣሬ መኖሩን የተናገሩት ኮሚሽነር ዘይኑ፤ በገንዘቡ መሳሪያ በመግዛትና በማስገባት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለመረጋጋት ለመፍጠር የታለመ መሆኑን ጠቁመዋል። የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚፈጸም አሻጥር እንደሚመስልም ነው የተናገሩት። ደሴ አካባቢ 24 ሚሊዮን ብር መያዙን አውስተው፤ ተጠርጣሪዎቹ  "ከአንድ ባንክ አውጥተን ወደ ሌላ ባንክ ልናስገባነው" የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም አካሄዱ ህገ-ወጥነት ያለው በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ህብረተሰቡ ከፖሊስና ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ወንጀለኞችን በማጋለጥ ዘመቻው እንዲጠናከር እንደዚህ ቀደሙ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም