በአዲስ አበባ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ገቡ

145

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21 /2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ቂርቆስ ፣አራዳና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ላይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ፕሮጀክት ምረቃት ሥነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

በተሰራው ስራ ክፍለ ከተሞቹን በኔትወርክ ለማስተሳሰር የተቻለ ሲሆን ክፍለ ከተሞቹ በቴክኖሎጂው ታግዘው የተቀናጀ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ተብሏል።

አገልግሎት ፈላጊዎች የሚወስድባቸውን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ለመቀነስ የመሰረተ ልማት ዝርጋታው የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ሰርሞሎ እንደተናገሩት፤ የተዘረጋው መሰረተ ልማት የኢንተርኔት፣ የቁጥጥር ካሜራ፣ የዋይፋይ አገልግሎትና የወረፋ ማስጠበቂያ አሰራርን ያካተተ ነው።

በፕሮጀክቱ በ46 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በመዲናዋ ለሚገኙ 18 ወረዳዎች የኔትወርክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በከተማው የሚገኙ 2 ሺህ ሃላፊዎችና አስፈጻሚዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የኢሜል ልውውጥ እንዲያደርጉና በቪዲዮ የታገዘ ስብሰባ እንዲያካሄዱ የሚያስችል ፕሮጀክት ተጠናቆ ዝግጁ መሆኑን አክለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን ሙሃመድ በበኩላቸው "ሚኒስቴሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተመረጡ ከተሞች የመንግስት አገልግሎቶችና የንግድ ስርዓቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ ነው" ብለዋል።

የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ሲሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ የአሁኑ ፕሮጀክት የዚህ ጥረት አካል መሆኑን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ዓለም በቴክኖሎጂ በመተሳሰር ወደ አንድ መንደር እየመጣች በመሆኑ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ መሰል ፕሮጀክቶች ወሳኝ እንደሆኑ አስገንዝበዋል።

ጥራትና ደህንታቸው የጠበቁ ፕሮጀክቶችን ለማልማትና ለማበልጸግ በጋራ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

"ዛሬ የተመረቁት ፕሮጀክቶች ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ሙስናን ለመከላከልና የክትትል ስራውን ለማዘመን ይረዳሉ" ብለዋል።

አዲስ አበባን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከተማ አስተዳደሩ እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።

ለፕሮጀክቶቹ እውን መሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ ክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ተቋማት የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

ኤጄንሲው ከዚህ ቀደም በአምስት ክፍለ ከተሞች ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን የዛሬዎቹን ጨምሮ በስምንት ክፍለ ከተሞችና 116 ወረዳዎች አገልግሎቱን በመስጠት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም