በአምስት ወር ውስጥ ከ18 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል- መምሪያው

ወልድያ፣ታህሳስ 21/ 2013 (ኢዜአ)ባለፉት አምስት ወራት ከ18 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን የሰሜን ወሎ ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ መምሪያ አስታወቀ። 

"ከመንግስት በተደረገላቸው ድጋፍ በመታገዝ ወደ ስራ የገቡ ወጣቶችም ውጤታማ ለመሆን እየተጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመምሪያው የኢንተርፕራይዞች ልማት ቡድን መሪ አቶ አጽብሐ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ በጀት አመት የስራ መስኮችን በመለየት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

"ባለፉት አምስት ወራት 18 ሺህ 120 ስራ አጥ ወጣቶችን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ ስልጠናና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች እንዲሰማሩ ተደርጓል" ብለዋል።

ወጣቶቹ በብረታ ብረትና እንጨት ስራ፣ በልብስ ስፌት፣ በአናፂነትና ግንበኛነት፣  በአትክልትና በፍራፍሬ ልማት፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።

መነሻ ካፒታል ለሌላቸው 25 ኢንተርፕራይዞች ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም 38 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

"ለበጀት ዓመቱ ለስራ ፈጠራ የሚያገለግል 70 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የተዘዋዋሪ ብድር በጀት ተይዞ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው" ብለዋል።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በዞኑ በበጀት አመቱ ለተመዘገቡ 75 ሺህ ስራ አጥ ወጣቶች ደረጃ በደረጃ የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

በዞኑ በዚህ አመት የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል የወልድያ ከተማ ነዋሪ  የሺዋ ጌታቸው "አምስት ሆነን ተደራጅተን  በልብስ ስፌት ስራ ተሰማርተናል" ብላለች።

የማህበሩ አባላት በመንግስት በኩል በልብስ ስፌት ሙያ የስድስት ወር ስልጠና፣ የስፌት ማሽንና ሌሎች ቁሳቁሶች ተሰጥቷቸው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግራለች።

"በአረብ ሀገር ስንከራተት ኑሬ ባዶ እጄን ብመለስም አሁን ላይ መንግስት ባደረገልኝ ድጋፍ ወደ ስራ በመግባቴ ደስተኛ ነኝ፤ በቀጣይ ሰርቼ ራሴንና ሀገሬን ለመጥቀም እጥራለሁ" ብላለች።

"በሐምሌ 2012 ዓም አጋማሽ  ሁለት ሆነን ተደራጅተን በተደረገልን የ25 ሺህ ብር ብድር በመታገዝ በፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ ገብተናል" ያሉት ደግሞ አቶ ጥላሁን መላኩ ናቸው።

የሳሙና ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን የገለጹት አቶ ጥላሁን ምርታቸውን ለማሳደግ እየተጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም