በብሔራዊ ደህነንት ምክር ቤት በተዘጋጀ የምርጫ ፀጥታ ዕቅድ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

82

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ) በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በተዘጋጀው አገር አቀፍ የምርጫ ፀጥታ ዕቅድ ላይ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት እየተወያዩ ነው።

ዕቅዱ የተዘጋጀው በተያዘው ዓመት የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒ፣ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማስቻል ነው።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በሚመሩት የምርጫ ፀጥታ ዕቅድ የምክክር መድረክ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

በመድረኩ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የጠቅላይ አቃቤ ሕግና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊዎች እንዲሁም የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ርዕሳነ መስተዳድርሮችና ከንቲባዎች፣ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች፣ ፖሊስ ኮሚሽነሮችና ጠቅላይ አቃቤያነ ሕጎች ተገኝተዋል።

የምርጫ ፀጥታ ዕቅዱ በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ የሚካሄደውን 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሠላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ለማድረግ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ለምታካሂደው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ፀጥታ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ወይዘሪት ብርቱካን ውይይቱን ሲከፍቱ ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በአገራዊ የምርጫ ጸጥታ ዕቅዱ መሰረት ክልሎች የራሳቸው ዕቅድ ያላቸው በመሆኑ በዚሁ ላይ በጋራ ለመስራት መነጋገር በማስፈለጉ እንደሆነም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም