ለችግር ፈቺ የተማሪዎች ፈጠራ ሥራዎች ድጋፍ ይደረጋል…. የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

5835

ጅማ ሀምሌ 14/2010 በተማሪዎች ከሚሰሩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች መካከል ችግር ፈቺ የሆኑትን በመለየት ድጋፍ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

 ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተመራቂ ተማሪዎች የተሰሩ የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡

በሚኒስቴሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የገበያ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እንድሪስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት መስሪያቤታቸው የፈጠራ ስራዎች ለአገር ጥቅም እንዲውሉ ትኩረት ስጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

በተማሪዎች ተሰርተው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ፈቺነታቸው ለሚመረጡ የፈጠራ ሥራዎች በ2011ዓ.ም ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር የገንዝብ ድጋፍ በማድረግ ወደ ተግባር የሚገቡበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ መሆኑንም ለእዚህ በማሳያነት ገልጸዋል፡፡

ለፈጠራ ሥራው ድጋፍ የሚደረገው ገንዘብ አዲስ በተዘጋጀው መመሪያ መሰረት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ መመሪያውን በሚመለከተው አካል ለማጸደቅ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ትስስር ዳይሬክተር አቶ ሸዋንግዛው ወርቅአገኘሁ በበኩላቸው በተማሪዎች የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለምረቃ አገልግሎት ከመዋል ባለፈ ትኩረት እንደማያገኙ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች የተሰሩ ፈጠራ ላይ ያተኮሩ የምርምር ስራዎችን በመለየት ከባለድርሻ አካላት ጋር የማስተዋወቅ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በእዚህም የፈጠራ ባለቤቶች ተደግፈው በግል ወደማምረት ተግባር እንዲገቡና ቀጣሪ መስሪቤቶችም ችሎታ ያላቸውን ምሩቃን በመቅጠር  ለአገርና ለህዝብ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን እንዲሰሩ ዕድል የሚያገኙበትን አሰራር በመከተል ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር የመጡት ኢንጂነር ለምለም ድጋፉ በበኩላቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የ2010 ዓ.ም ተመራቂዎች የተሰሩት የፈጠራ ሥራዎች ተገቢውን ድጋፍ ካገኙ ችግር ፈቺ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

“በተማሪዎች የሚሰራው የምርምር ሥራ ወጭ ቆጣቢ፣ ከአካባቢ ከሚገኝ ግበአት በቀላሉ የሚሰራና በትንሽ የሰው ኃይል የሚተገበር  መሆኑ በገበያ ተፈላጊ ያደረገዋል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች አላማቸው ለመመረቅ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታትም ጭምር ሊውሉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

አገልግሎት የማይሰጡ የፕላስቲክ ምርቶችን ከሌሎች የግንባታ ግብአት ጋር  በመጠቀም የመንገድ ንጣፍ መስራት የሚያስችል የፈጠራ ስራ መስራቱን የገለጸው ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህድስና የተመረቀው አበዱላዚዝ ትግስቱ ነው።

የፈጣራ ሥራው ወደ ምርት እንዲሸጋገር ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር የሚተዋወቅበትን መድረክ መፍጠሩ የበለጠ ለመስራት አንዳነሳሳው ተናግሯል፡፡

ተመራቂ ፍቅርተ ዘገየ በበኩሏ በቡድን በመሆን ያከናወኑት የፈጠራ ሥራ ከወዳደቁ ፕላስቲኮች የተለያዩ የግንባታ ግበአቶችና የቤት ቁሳቁስ ማምረት የሚያስችል መሆኑን ተናግራለች፡፡

በቡድን በመሆን የሰራነው ፈጠራ ሥራ ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላይ የተወገዱ የፕላስቲክ ምርቶች በቀላሉ የማይበሰብሱ በመሆኑ በግብርና ምርት ላይ የሚያደርሱትን ተጽእኖ እንደሚቀንስ ገልጻለች ፡፡

ትናንት በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጀውና ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው የምክክር መድርክ ላይ 14 የፈጠራ ሥራዎች ለእይታ መቅረባቸውን የዩኒቨርሲቲውን መረጃ ያመለክታል ነው።