ቤጉህዴፓ አገራዊ ለውጡን ተቀብለው ክልሉን ሊመሩ በሚችሉ አመራሮች ራሱን እንደሚያደራጅ አስታወቀ

87
አሶሳ ሀምሌ 14/2010 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ተቀብለው ክልሉን በለውጥ ሂደት ሊመሩ በሚችሉ አመራሮች ራሱን እንደሚያደራጅ አስታወቀ። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የድርጅቱንና የክልሉን መንግስት የሥራ አፈጻጸም በአሶሳ ከተማ የገመገመበት መድረክ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡ ፓርቲው የግምገማ መድረኩን አስመልክቶ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ አገሪቱን ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ የሚያደርስ ነው፡፡ በመሆኑም ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው ፓርቲው የድርሻውን ለማበርከትና በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው በዚህ የለውጥ ሂደት የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ፓርቲው በትኩረት ይሰራል፡፡ በክልሉ በርካታ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች እንደሚኖሩ የጠቆመው መግለጫው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ያለውን መልካም አብሮነት ለመሸርሸር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንና ፓርቲውም ይህን ለማክሸፍ እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡ ቤጉህዴፓ በክልሉ የሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ያካተተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክሮ እንደሚሰራም ነው የገለጸው፡፡ የክልሉ አመራር ምደባን በተመለከተም በቀጣይ ህዝብን በማስተቸት የተጀመረውን አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ማስቀጠል በሚችሉ አመራሮች እንደሚያደራጅም አመልክቷል፡፡ በክልሉ የሚስተዋለውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት፣ ደካማ የስራና የቁጠባ ባህል ለማስተካከል መስራት የፓርቲው ቀጠይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በድርጅቱ መሪነት በክልሉ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች ቢኖሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የተፈጠሩ ችግሮች የፓርቲው ድክመት ውጤቶች በመሆናቸው ክፍተቶቹን ለማረም ቤጉህዴፓ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ተመልክቷል፡፡ ፓርቲው ለሁለት ቀን ባደረገው ግምገማ አንድ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልን ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ ያደረገ ሲሆን አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴው አባልን ደግሞ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲነሱ ወስኗል። በክልሉ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር በሰው ሕይወትና አካል ላይ ለደረሰው ጉዳት ፓርቲው የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጾ ድርጊቱ  ዳግም እንዳይከሰት ማዕካላዊ ኮሚቴው ከመላው የክልሉ ህዝብ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም