በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከደረጃ 'ሐ' ግብር ከፋዮች 9 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው

61
ሰቆጣ ሀምሌ 14/2010 በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የተጣለባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡ ከደረጃ ‘ ሐ’ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ከሃምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ገቢዎች ፅህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በዝቋላ ወረዳ በፅፅቃ ከተማ በሽቀጣ ሸቀጥ ንግድ የተሰማሩት አቶ አለማየሁ እንደሻው ባለፈው አመት ግብር በወቅቱ በመክፈል ግዴታቸውን መወጣት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው አመትም በሰሩት ልክ የተጣለባቸውን 2 ሺህ 800 ብር በወቅቱ መክፈላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሌላው ግብር ከፋይ ነጋዴም በሚሰበሰበው ግብር ልክ ለሃገር ልማት አገልግሎት የሚውል መሆኑን በመገንዘብ የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በሰቆጣ ከተማ በሴቶች ውበት ሳሎን የተሰማራችው ወጣት ሃና መርሻ “ባለፈው አመት የተጣለብኝ የ3 ሺህ ብር ግብር ቅሬታ አቅርቤ  ተስተካክሎልኝ መክፈል ችያለሁ፤ ዘንድሮም የተጣለብኝን የ1 ሺህ 500 ብር ግብር በወቅቱ በመክፈል ግዴታየን ተወጥቻለሁ’’ ብላለች፡፡ “በዞኑ ከሐምሌ 1 ቀን  2010 ዓ.ም ጀምሮ ከ5 ሺህ 474 በላይ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ከ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የዞኑ ገቢዎች ጽህፈት ቤት የግብር ትምህርት ኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እሸቱ ደመቀ ናቸው፡፡ እስካሁንም በዞኑ በተከፈቱ 34 ጊዜያዊ የግብር መክፈያ ጣቢያዎች  3 ሺህ ያህል ነጋዴዎች ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈላቸው 4 ሚሊዮን 425 ሺህ ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ እስከ ሃምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስም እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ብሄረሰብ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን ጨምሮ በሁሉም ምድቦች ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ በክልሉ ሁለተኛ ደረጃ በመውጣት ተሸላሚ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም