ከምርጫው በላይ የሠላም ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል – የፖለቲካ ፓርቲዎች

1550

ታህሳስ 16/2013(ኢዜአ) ከምርጫው በላይ አገራዊ የሠላም ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ። 

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩላቸው ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ ከማስቀመጥ ባለፈ ምርጫውን ማራዘም ተገቢ አይደለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ዓመት የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር እንደሚታይና ሌሎችም ምርጫውን ማካሄድ አያስችሉም ያሏቸውን ጉዳዮች አቅርበዋል።

የምርጫ አስፈፃሚ አመራረጥን በተመለከተም ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ምርጫዎች ለገዥ መንግስት የሚወግኑ ግለሰቦች እንዳይመለመሉ ሲሉ አንስተዋል።

ምርጫ ቦርድ ቸል ሊላቸው አይገባም ያሏቸውን ጉዳዮችም ጠቅሰዋል።

የፓርቲዎቹ ተወካዮች ላነሷቸው ጥያቄዎችና ላቀረቧቸው አቤቱታዎች በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ዛዲግ አብርሃ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አገራዊ ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው የአስፈፃሚዎችን ምልመላ በተመለከተ ገለልተኛ ሰዎች እንዲሆኑ ተገቢው ጥንቃቄ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ሠላምን በተመለከተም ምርጫ ቦርድ የራሱን ስራ፤ መንግስትም የፀጥታውን ጉዳይ ይሰራሉ ብለዋል።

የምልመላው ሂደት ለፓርቲዎች ግልጽ እንደሚሆንና አስተያየት እንደሚሰጡበትም ተናግረዋል።