6ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 28 እንዲካሄድ በጊዜያዊነት ቀን ተቆረጠለት

1522

አዲስ አበባ ታህሳስ 16/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የምታካሂደው 6ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 28 እንዲካሄድ በጊዜያዊነት ቀን ተቆረጠለት ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንደሮውን አገራዊ የምርጫ ለማካሄድ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አደርጓል።

የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው የተቀመጠ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 05 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሆን በረቂቁ ተመላክቷል።

ግንቦት 28 እና 29 ቀን 2013 ዓ.ም ለአገር አቀፍ ምርጫ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ውጤት የሚገለጽባቸው ቀናት እንዲሆኑም በረቂቁ ተቀምጧል።

ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ የምርጫ ውጤት የሚገለጽበት ጊዜ እንደሚሆንም የቦርዱ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አመልክቷል።

የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ከየካቲት 08 ቀን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ተቀምጧል።

የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ በጊዜያዊነት ቀን ተቆርጦለታል።

ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው የትግራይ ክልልን እንደማይመለከትም ገልጿል።