የኢንዱስትሪ ፓርኮች ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ጥናት ተዘጋጀ

153

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ)የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል የስፓሻል ፕላን ጥናት ማዘጋጀቱን ገለፀ።

ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መቅረፍ ያስችላል ባለው የመጨረሻ ጥናት ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላትጋር ተወያይቷል፡፡

ጥናቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ በማድረግ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ፓርኮቹ ከከተሞች ልማት ጋር ተሳስረው መቀጠል የሚችሉበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነም ተገልጿል።

ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚመሩበት ስፓሻል ጥናት ላይም ገለጻ ተደርጓል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ለኢዜአ እንዳሉት ረቂቅ ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ የመሰረተ ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በስፋት የሚመልስ ይሆናል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው ጥናቱ መነሻና መድረሻን የሚያሳይ ስልታዊ ዕቅድ እንደሆነና መንግስት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ለመደገፍና ለማገዝ ያመቻቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግስት ከዚህ በኋላ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አይገነባም በሚል የሚሰራጨው መረጃ ትክክል እንዳልሆነም አመላክተዋል።

የጥናቱ አስተባባሪ ወይዘሮ ፋናዬ ታደሰ በበኩላቸው "ጥናቱ የሁሉንም ኢንዱስትሪ ፓርኮች የ10 ዓመት ዕቅድ ያካተተና የኢንዱስትሪውን ልማት ማፋጠን በሚቻልበት መንገድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ከተሞችና ኢንዱስትሪዎች ተሳስረው መሄድ የሚችሉባቸው መንገዶች በጥናቱ መዳሰሳቸውንም አብራርተዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የተማረ ሀይል በማቅረብ እንዲሁም ጥናቶች እንዲሰሩ በማድረግ የሚተሳሰሩበት መንገድ የታሰበበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ከኮርፖሬሽኑ ባለፈው አመት  በነበረው ቆይታ  በአገሪቷ ከሚገኙ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰባቱ በስራ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም