የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናት በአመክሮ ተለቀቁ

61

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናት ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ በአመክሮ መለቀቃቸውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናት የፍርድ ሂደታቸው በሌሉበት የታየ እና የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው የሞት ቅጣት ተጥሎባቸው ነበር፡፡

የጣልያን ኤምባሲ የቀድሞው ደርግ ባለስልጣናት የነበሩት ሰዎች በተመለከተ በሰጠው ኦፊሲላዊ ገለጻ ግለሰቦቹ ለረጅም ዘመናት ነፃነታቸው ተገድቦ የቆዩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከኤምባሲው ምንም አይነት ድጋፍ አይደረግላቸውም ነበር።

በመሆኑም ከቤተሰቦቻቸው በሚላክላቸው ቀለብ በአንድ ቅጥር ግቢ በተወሰነ ስፍራ ብቻ ተወስነው ከእድሜ መግፋት እና ከተፈጥሮ ህመም ጋር በተገናኘም ተገቢውን ህክምና ለማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው መቆየታቸውን ኤምባሲው ማረጋገጡን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

የእርቀ ሰላም ኮሚሽንም ግለሰቦቹ በህግ አግባብ ተለቀው ቤተሰቦቻቸውን እንዲቀላቀሉ ለመንግስት ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን ያስታወሰው መግለጫው፤ በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ ቆይተው የነበሩ የቀድሞ ደርግ አመራሮችም ከ10 ዓመታት በፊት ከእስር ወጥተው ከማህበረሰቡ ጋር እየኖሩ እንደሆነ ጠቅሷል።

በተቃራኒው በጣልያን ኤምባሲ ውስጥ ተወስነው ለ30 ዓመታት የቆዩት እነኚህ ሰዎች ከመደበኛው የእርምት ስፍራ ባልተናነሰ በተወሰነ አነስተኛ ቅጥር ግቢ ውስጥ ወደ ህክምና ተቋማት እንኳን መውጣት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ከመንግስትም ሆነ ከቆዩበት የኤምባሲ ቅጥር ግቢ አስተዳዳሪ ምንም አይነት እንክብካቤ እና ድጋፍ ሳያገኙ መቆየታቸው በእስር ቢቆዩ ኖሮ ከሚፈጠርባቸው የመብት ገደብ አንጻር ቢበዛ እንጂ የሚያንስ እንዳልሆነ ግንዛቤ መወሰዱን አመልክቷል።

በመሆኑም መንግስት ከዚህም በላይ እነኚህን ሰዎች ከዚህ በኋላ ነጻነታቸውን ገድቦ ማቆየት የፍትህ አላማን ከማሳካትም አንጻር የሚጨምረው ውጤት የማይኖር በመሆኑ፣ ከፍርደኞቹ እድሜ እና የጤና ሁኔታ አንጻር የሰብዐዊነት እይታን ከግምት በማስገባት በግለሰቦቹ ላይ ተወስኖ የነበረውን የሞት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀየር ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሃሳብ ማቅረቡን ገልጿል።

በዚሁ ሃሳብ መሰረት ፕሬዚዳንቷ ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት እንዲለወጥ መወሰናቸውን አስታውሷል።

በዚህም መሰረት መንግስት ግለሰቦቹ ካሉበት ስፍራ መውጣት ስለሚችሉበት ሁኔታ ከህግ ማዕቀፍ እይታ አንጻር አስፈላጊውን ጥናት አድርጎ ግለሰቦቹ እስካሁን በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ነጻነታቸው ተገድቦ መቆየቱ አስተማሪነት ያለው መሆኑ ከግምት ገብቶ በአመክሮ እንዲለቀቁ አቤቱታ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የቀረበውን አቤቱታ ተቀብሎ ግለሰቦቹ በአመክሮ እንዲለቀቁ ወስኗል።

በዚህ መሰረት የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናት ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ በአመክሮ መለቀቃቸውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም