በዞኑ ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ

76
ሚዛን ሀምሌ 13/2010 በቤንች ማጂ ዞን  መንግስታዊ ተቋማት ተገቢውንና የተሟላ አግልግሎት እንዲሰጡ በሰው ኃይልና በቁሰቁስ ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ በዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ አዘጋጅነት የመንግስት ሰራተኞች ሳምንት በዓል በሚዛን ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች  ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ከተሰታፉት መካከል በዞኑ ከተማ ልማት መምሪያ የምርታማነትና ገበያ ጥራት የሥራ ሂደት አስተባባሪ  አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት ተቋማት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት የማይችሉት  በሰው ኃይልና ግብዓት አለመሟላት ዋናው ምክንያት ነው፡፡ የተቋማቸው የሰው ኃይል በትንሹ ከሚያስፈልገው ውስጥ የተሟላው 19 በመቶ ብቻ እንደሆነ ገልጸው በዚህም ተገቢውንና የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ " የቁሳቁስ  አለመሟላትም ፈጻሚ ባለሙያው ሙሉ በሙሉ አቅሙን አሟጦ ሥራ ላይ እንዳያውል ያደርገዋልም "ብለዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ በተገቢው እንዲወጡ በሰው ኃይልና በቁሰቁስ ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ በዞኑ የማህበራዊ ዋስትና ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ ቀኒቶ ገብረ ማርያም በበኩላቸው ተቋማቸው የተለያዩ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እጥረት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ " የግብዓት ችግሩም ለተገልጋዮች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚፈለገው  ማድረስ እንዳይቻል አድርጓል "ብለዋል፡፡ ስራን የሚያቀላጥፍ  አደረጃጀቶችን በአግባቡ መተግበር ውጤታማ እንደሚያደርግ የተናገሩት ደግሞ በባቹማ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ባለሙያ የሆኑት አቶ አንዱዓለም ጥላሁን  ናቸው፡፡ በመንግስት በኩል እነዚህን ጉድሎቶች ለማስተካከል  የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍም የድርሻቸውን እንደሚወጡም ሰራተኞቹ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ የሪፎርም ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሰዒድ በበኩላቸው "ተቋማት ለተገልጋዮች ፈጣንና ፍትሀዊ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል  አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ተገቢ ነው" ብለዋል፡፡ በቤንች ማጂ ዞን የተለያዩ  ተቋማት የሰው ኃይል ውስንነት እንዳለባቸውና ይህም ለመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተገልጋዩ ቅሬታ ከሚያሰማባቸው ጉዳዮች ሌላው ተደጋጋሚ ስብሰባ መሆኑን ጠቁመው "አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በስራ ሰዓት ጊዜያቸውን ለሥራ ብቻ ማዋል ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡ ጉድለቶችን ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግም ተመልክቷል፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ሳምንት በዞኑ ለ8ኛ ጊዜ ትናንት በፓናል ውይይት፣ በጥያቄና መልስ የተከበረ ሲሆን በዕለቱም የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ተቋማትና ሠራተኞች ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በቤንች ማጂ ከ13ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉ ከዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመልክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም