ኤጀንሲው አዲስ የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ አደረገ

2124

አዳማ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጀትና ስርጭትን ለማዘመን የሚያስችል አዲስ የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ ማድረጉን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው አዲስ ባበለጸገው የተቀናጀ የመረጃ አያያዝና አስተዳደር ስርዓት አጠቃቀም ከአስር ክልሎችና ከሁለት የከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ ባለድርሻ አካላት በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀን የሚቆይ የግንዛቤ ስልጠና እየሰጠ ነው ።

ትግበራው የመረጃ ስርዓት አስተዳደር፣ የመረጃ አሰባሰብና የስርጭት ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችል መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ ተናግረዋል ።

ስርአቱ ተጠቃሚዎች ባሉበት ሆነው የሚፈልጉትን መረጃ ማግኘት የሚችሉበት መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ የተጠቃሚዎቸ የመረጃ መረብ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

“ስርዓቱ ከማዕከል ጀምሮ እስከ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ትክክለኛ፣ ወቅታዊ፣ ታእማኒ፣ ተፈላጊና ዘርፈ ብዙ መረጃዎችን መዝግቦ የሚይዝ ነው” ያሉት ደግሞ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ ናቸው።

የህዝብና ቤት ቆጠራ፣ የግብርና፣ ጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ነባር መረጃዎች ወደ ስርዓቱ መግባታቸውን አመልክተዋል።

“ክሌሎችን ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ እየተደረገ ነው “ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉልና አፋር ክልሎች ወደ ተቀናጀ የመረጃ ስርዓት ገብተው እየተጠቀሙ መሆኑን ገልፀዋል ።

ሱማሌና ሐረር ክልሎችም በቅርቡ ወደ ስርዓቱ እንደሚገቡ አመላክተዋል።

ጋምቤላ፣ ትግራይና ሲዳማ ክልሎችንም ወደ ሰርአቱ ለማሰገባት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በስርአቱ አጠቃቀም ላይ የሚኖር የአቅም ውስንነትን ከወዲሁ ለመቅረፍ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

“አዲሱን የመረጃ ስርዓት ተከትሎ የበለፀገው የመረጃ መረብ እስከ 74 ሚሊዮን መረጃዎችን በቀጥታ የማሰራጨት አቅም አለው” ብለዋል።

በተመሳሳይ በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የስርዓተ ፆታ ያለበትን ሁኔታ አመላካች መመሪያና መነሻ ሃሳቦችን የያዘ ሰነድ በኤጄንሲው ይፋ ተደርጓል ።