በሳውላ ከተማ አስፓልትን ጨምሮ ከ57 ኪሎሜትር በላይ መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቃ

110
አርባምንጭ ሐምሌ 13/2010 በጋሞጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በህብረተሰቡና በመንግስት ድጋፍ ከ57 ኪሎሜትር በላይ የአስፓልት፣ የድንጋይ ንጣፍና የጠጠር መንገድ ተገንብቶ አገልግሎት መሰጠት ጀመረ፡፡ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ስራስኪያጅ አቶ ተመስገን አየለ እንደገለጹት በሳውላ በተለይ የአስፓልት መንገድ ባለመኖሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ህዝብና መንግስት በጋራ ባደረጉት 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሲሰራ ቆይቶ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት ከበቃው መንገድ ከ2 ኪሎሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም 40 ኪሎሜትር በላይ የጠጠር መንገድ እና ከ15 ኪሎ ሜትር በላይ ደግሞ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ተሰርቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ከዚህም ሌላ  ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈውና በግንባታ ላይ የሚገኘው የሳውላ ማጂ እና የካምባ ሳውላ መንገድ ፕሮጀክቶች ለአካባቢው ዕድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ የህዝቡ ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ተጨማሪ የመንገድ ግንባታ ስራ ይቀጥላል ተብሏል፡፡ በሳውላ የዮጫ ክፍለ ከተማ  ነዋሪ አቶ ታደለ ከበደ ለከተማው የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ባለመሰራቱ ቅሬታ አሳድሮባቸው እንደነበር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ "ሳውላ ከተማን በጋራ እናልማ"  በሚል መሪ ሀሳብ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመሆን ባደረገው ድጋፍ መንገዱ ተገንብቶ ተጠቃሚ መሆን በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ የመንገዱ መገንባት  ለማህበራዊ ግንኙነታቸው  ምቹ ፈጥሮላቸዋል፡፡ የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ተስፋሁን ታደለ በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ ለእናቶች በወሊድ ጊዜ ወደ ጤና ተቋም በአንቡላንስ ፈጥኖ ለማድረስ እንደሚያመች ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ለከተማው ውበት መሆኑንና በቀጣይም ለልማቱ  ከመንግስት ጎን ለመቆም ይበልጥ እንዳነሳሳቸውም ጠቁመዋል፡፡ "ከተማው ሙሉ በሙሉ የአስፓልት መንገድ ባለመኖሩ ክረምት ላይ በጭቃ፣ በጋ ላይ ደግሞ በአቧራ ስንቸገር ቆይተናል" ያሉት የቦላ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ቦጋለ ዛዋ ናቸው፡፡ መንግስት ብቻውን በሁሉም መስክ የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት ስለሚያዳግተው ስራውን ለማፋጠን የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ መንገዱ ተገንብቶ የነበረባቻው ችግር መቃለሉን ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም