ለሕወሃት የጥፋት ቡድን ገንዘብ በመደገፍ የተጠረጠሩት የሙለር ሪልስቴት ባለቤትና ሁለት ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

92

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2013 (ኢዜአ) የሕወሃትን የጥፋት ቡድን በገንዘብ በመደገፍ በወንጀል የተጠረጠሩት የሙለር ሪልስቴት ባለቤትና ሁለት ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

በወንጀሉ የተጠረጠሩት አቶ ሃይሌ መዝገቡ፣ የሙለር ሪልስቴት ባለቤት የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ  እና አቶ ሳሙኤል አባዲ ናቸው።

ፖሊስ እነ አቶ ሙሉጌታ ተስፋ ኪሮስን ጨምሮ ሶሰት ተጠርጣሪዎች ላይ ከዚህ በፊት ፍርድ ቤቱ በፈቀደው 10 ተጨማሪ ቀናት ያከናወነውን ስራ አብራርቷል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች ተጠርጣሪዎቹ ለህወሓት ቡድን ሪፎርም ማጠናከሪያ በሚል ሽፋን አባላትን ሲያደራጁ እንደነበር መረጃ ማግኘቱንም ፖሊስ አስታውቋል።

ለህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን ድጋፍ የሚውል ገንዘብ በባንክ ማስገባታቸውንም ማስረጃ ማግኘቱን መርማሪ ፖሊስ መግለጹ የሚታወቅ ነው።

በአዲስ አበባ ልዩ ዞን የህወሓት ፅህፈት ቤት ለመመስረት በሚል ሽፋን ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ እንደነበረም ማስረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።

በተለይም የሙለር ሪልስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ ብር በማሰባሰብ ወንጀሉ እንዲፈጸም ድጋፍ ማድረጋቸውን አረጋግጫለሁ ነው ያለው ፖሊስ።

ፖሊስ በሌላኛው  ተጠርጣሪ አቶ ሳሙኤል አባዲ ላይም  የህወሓት ቡድን አባላትን ዝርዝር የያዘ በሰንጠረዥ የተዘጋጀ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ማስረጃ ማግኘቱን ገልጿል። 

በተጠርጣሪዎቹ ላይም ቀሪ ምርመራ ለማካሔድ ፍርድ ቤቱን 14 ተጨማሪ ቀን ጠይቋል።

የሙለር እሪልስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ "እኔ ነጋዴ ነኝ እንጂ ፖለቲከኛ አይደለሁም ለማንም ድጋፍ አላደረግኩም" ሲሉ ተከራክረዋል።

የግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱም 12 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለታሕሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም