በጆርጂያ በሚካሄደው የቼስ ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ሴት የቼስ ስፖርኞች ተለይተው ታወቁ

78
አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2010 በመጪው መስከረም በጆርጂያ ባቱሚ ከተማ በሚካሄደው 43ኛ ዓለም አቀፍ  ቼስ ኦሎምፒያድ ላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን የሚወክሉ ሴት ተወዳዳሪዎች ተለይተው ታውቀዋል። የኢትዮዽያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ እንደተናገሩት ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው የሚሳተፉ አምስት ሴት ተወዳዳሪዎች ተለይተዋል። ተወዳዳሪዎቹን ለመለየት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከሐምሌ 10 ቀን 2010 ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የቼስ ውድድር ለሁሉም የቼስ ስፖርተኛ ክፍት የተደረገ ነው። በዚህ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ለመለየት በተዘጋጀ የቼስ ውድድር 55 ወንዶችና 16 ሴት ስፖርተኞች እየተካፈሉ ናቸው። በሴቶች ምድብ ከሚወዳዳሩ ስፖርተኞች መካከል ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አምስት ሴት ስፖርተኞች ተለይተው ታውቀዋል። ልደት አባተ በቀዳሚነት ስትመረጥ፤  ፌቨን ገብረመስቀል በሁለተኛነት የብሄራዊ ቡድኑ አባል ሆነው ተመርጠዋል። እንዲሁም ሩት ለይኩን፣ መርሃዊት ብርሃነና  አስቴር መላክ ደግሞ ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘው በማጠናቀቃቸው የብሄራዊ ቡድኑ ኣባል ሆነው ተመርጠዋል። በወንዶች በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ የቼስ ስፖርተኞች ነገ የሚታወቁ ይሆናል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም