ኢትዮጵያ ለሱዳንና ጂቡቲ ከሸጠችው የኤልክትሪክ ኃይል ከ81 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

91
ሐምሌ 13/2010 ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው  በጀት ዓመት ለሱዳንና ጂቡቲ ከሸጠችው  የኤሌክትሪክ ኃይል 81 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ማግኘቷን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ከሁለቱ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሽያጭ ከ86 ሚሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት  ቢታቀድም በበጀት ዓመቱ የተገኘው  81  ነጥብ 6 ሚሊየን  ዶላር ነው፡፡ ለሁለቱ ሀገራት በሰዓት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ኪሎ ዋት  በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ታቅዶ  በሰዓት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ኪሎዋት  በላይ መሸጡንም ነው ኃላፊው ያብራሩት። በበጀት ዓመቱ ለሱዳን ብቻ በሰዓት 864 ሺህ ኪሎዋት  የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 43 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ  ታቅዶ  በሰዓት 949 ሚሊየን 905 ሺህ 712 ኪሎ ዋት  በመሸጥ 47 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ለጂቡቲ ደግሞ በሰዓት 648 ሚሊየን ኪሎ ዋት  የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 43 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ለመሰብሰብ ቢታቀድም በሰዓት 515 ሚሊየን  556 ሺህ 66 ኪሎዋት  ተሸጦ  34 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል። ኃላፊው እንዳሉት የጂቡቲው አፈጻጸም ከእቅዱ ያነሰበት ምክንያት ሀገሪቱ  የኤሌክትሪክ ኃይል በምትፈልግ ጊዜ ብቻ የምትገዛ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርበት ወቅተ ሁለቱም ሀገራት የኤሌክትሪክ ፍላጎታቸው እንደሚጨምርም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም