የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጎልበት ትምህርት ቤቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ

ድሬዳዋ ታህሳስ 13/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማጎልበት ትምህርት ቤቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም  ድሬዳዋ ቅርንጫፍ  የመልካም አስተዳደር ክበባትን በሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ መስርቷል፡፡

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አለማየሁ አድማሱ በወቅት  እንደገለጹት፤የመልካም አስተዳደር ክበባት በትምህርት ቤቶች መመስረታቸው ሀገር   ገንቢና ተረካቢው  ትውልድ  የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን ከወዲሁ እንዲለማመዱ ያግዛሉ፡፡

በትምህርት ቤቶች ውስጥ በተማሪዎች መካከልየሚፈጠሩ  ቅሬታዎች ከሚመለከታቸው  አካላት ጋር በመወያየትና በመነጋገር መፍትሄ እንዲሰጥ ክበባቱ እንደሚረዱ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማጎልበት ትምህርት ቤቶች ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡

በሙከራ ደረጃ በድሬዳዋ ሁለት ትምህርት ቤቶች የተመሰረቱት የመልካም አስተዳደር ክበባት በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደሚስፋፉ ተቋሙ  መሰራቱን እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

የሣቢያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመልካም አስተዳደር ክበብ አባል ተማሪ ሸዋዬ ንጉሴ በሰጠችው አስተያየት፤ ''በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ችግሮችን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ክበቡ ያግዘናል'' ብላለች፡፡

ክበቡ ተማሪዎቹ በሥነ-ምግባር ታንጸው ስለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ይበልጥ እንዲረዱ የሚበጅ መሆኑን ተናግራለች፡፡

የእንባ ጠባቂ ተቋሙና መምህራን ክበቡ  የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ማገዝ እንደሚገባቸውም ጠቁማለች፡፡

በድሬዳዋ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተቋቋመው ክበብ አባል ተማሪ ሙስጠፋ ሁሴን በበኩሉ፤ የክበቡ መመስረት ተማሪው ግዴታውን እንዲወጣና መብቶቹ እንዲከበሩ ለማድረግ እንደሚያግዘው ገልጻል፡፡

ለተመሰረቱት ክበባት አባላት ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መቋቋሚያ አዋጅና የክባበቱ ቀጣይ ተልዕኮ ገለፃ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም