ምክትል ከንቲባዋ አመራሩ የማምረቻውን ዘርፍ ችግሮች ተናቦ እንዲፈታ አሳሰቡ

70

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አመራር በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚስተዋሉ ችግሮችን ተናቦ እንዲፈታ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ።

የአዲስ አበባ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው በውይይቱ የተሳተፉ የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎችም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ዘርዝረዋል።

የጥሬ ዕቃ፣ የገበያ ትስስር፣ የመስሪያ ቦታ፣ የክህሎት፣ የፋይናንስ አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን የዘርፉ ማነቆዎች ሲሉ ተነስተዋል።

ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እድገት መሰረት ለመጣል ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም ብለዋል።

ዘርፉ ለበርካታ የሰው ሃይል የስራ ዕድል በመፍጠር የማይተካ ሚና ያለው ቢሆንም ስራ ፈጣሪዎች በአሰራር ችግሮች ምክንያት ዘላቂ መሰረት እየጣሉ አለመሆኑም ተነስቷል።

በኢንተርፕራይዞች በኩል ያለው የአመለካከት ክፍተት፣ የስራ ባሕል አለመጎልበት፣ በአቋራጭ የመበልፀግ ፍላጎትና ሌሎችም ችግሮች በመድረኩ ተሰታፊዎች ተጠቅሰዋል።

የማምረቻውን ዘርፍ ስራ ፈጣሪዎች የመስሪያ ማሽን ችግር ለማቃለል በዚህ ዓመት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የሊዝ ፋይናንስ ብድር መዘጋጀቱን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር አቶ አስፋው አበበ የሊዝ ፋይናንስ ብድሩ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዘርፉ የሚቀርቡ የስልጠና፣ የመሰረተ ልማት፣ የመስሪያ ቦታ፣ የፋይናንስና ሌሎችም በትክክል ለሚፈለገው ዓላማ መዋላቸውን መመርመር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የግብዓት እጥረት ስለመኖሩ የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ "ዋናው ችግር እጥረት አይደለም፤ ያገኘነውን ግብዓት እንዴት ስራ ላይ አዋልን የሚለው ነው" ሲሉ ችግሩን በትኩረት አንስተዋል።

በአዲስ አበባ ብቻ ለመስሪያ ተብለው የተሰጡ ቦታዎች ተላልፈው በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ በመጠቆም የችግሩን ስፋት አመላክተዋል።

በመሆኑም አመራሩ ራሱን ከእነዚህ ችግሮች አፅድቶ የመደገፍ፣ ግብዓቶችን ለሚገባው አካል ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አለበት ብለዋል።

በብድር የሚቀርቡ ማሽኖችና ገንዘብ ማስመለስ ያልተቻለባቸውን ሁኔታዎች መለየት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዘርፉ የሚሰማሩ ስራ ፈጣሪዎች በወሰዱት ብድር ውጤታማ እንዲሆኑና የመስሪያ ቦታዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በቅንጅት መምራት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞችም በአቋራጭ ከመክበር አስተሳሰብ ወጥተው ሰርተው መለወጥን ማመን መቻል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ 20 ሺህ አምራቾች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም