በመተከል የጥፋት ቡድኑን ለመቆጣጠር ቤት ለቤት የማደን ሥራ ተጀመረ

153

አሶሳ፤ታህሳስ 12/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ልዩ ስልት ቀይሶ የጥፋት ቡድኑን ለመቆጣጠር ቤት ለቤት የማደን ሥራ መጀመሩ ተገለጸ። 

ሀገር አቀፍ ማህበረሰብ ተኮር የምክክር መድረክ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል በካማሽ ዞን መካከለኛ አመራር የሆኑት አቶ ዘቢድ ቡድና እንዳሉት የመተከል ዞን ጸጥታ ለማስተካካል ከፍተኛ ሥራ ተከናውኗል፡፡

ይሁንና  አሁንም በሰዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አመልክተው በዞኑ ኦነግ ሸኔ ዋነኛ የጸጥታ ስጋት ነው ብለዋል።

አቶ ዘቢድ በጁንታው ላይ የተወሰደው እርምጃ በክልሉ  ባሉ የጥፋት ቡድኖች ላይም ሊወሰድ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል፡፡

አቶ መሃመድ ከማል  የተባሉት የምክክር መድረኩ ተሳታፊ በበኩላቸው በአሶሳ ከተማ በ2010 ዓ.ም. ሰኔ ወር የተከሰተን ግጭት አስታውሰው፤ ህብረተሰቡ ለሠላም ባለው ቁርጠኝነት ችግሩ በአጭሩ መቀጨት ተችሏል ብለዋል፡፡

የመተከል ግጭት ረጅም ጊዜ ቢወስድም ግጭቱን ለማስቆም የተለያየ እርምጃ መወሰዱንም አውቃለሁ ነው ያሉት። 

እርምጃ ብወሰድም ችግሩ  አሁንም መኖሩን  ጠቅሰው ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢው አመራሮች በጉዳዩ መሳተፋቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

በአካባቢው ጽንፍ የረገጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸው፤በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው  የሃሰት ትርክቶችም ችግሩን እያባባሱት በመሆኑ ማስተካከል እንደሚገባም ተናግረዋል። 

የመተከልን ችግር በሚገባ የመለየት ሥራ አስቀድሞ አልተካሄደም ያሉት በአሶሳ ዞን የኩርሙክ ወረዳ አመራር አቶ አብዱልዋሂድ ሃመድ ለመፍትሄው ወረዳዎች ተቀናጅተው ክልሉን መደገፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የውይይት መድረኩን ከመሩት መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ የመተከል ግጭት መንስኤው ሃገራዊ ለውጡን በማይቀበሉ ሃይሎች የተቀነባበረ ነው ብለዋል፡፡

ለመፍትሔው ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

የጸጥታ ሃይሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ የጥፋት ቡድኑን እያስወገደ ነው ያሉት ምክትል ሃላፊው፤ የዞኑ ኮማንድ ፖስት ልዩ ስልት ቀይሶ ቤት ለቤት የጥፋት ቡድኑን ማደን መጀመሩን አስታውቀዋል።

ህብረተቡም የጥፋት ቡድኑን እንዲያጋልጥ ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን በማመልከት፤ በአጭር ጊዜ ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮች መተከልን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር  የሚተላለፉ  ሀሰተኛ መልዕክቶችን መታገል እንደለባቸውም ነው አቶ ሙሳ ያስገነዘቡት።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በኦነግ ሸኔ አባላት ላይ እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ ተከትሎ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚገቡ የጥፋት ቡድኑን አባላት አድኖ ለመያዝ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሠላም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ስራ አመራር ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ አዱኛ በቀለ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ  መተከልን ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱን ሠላም ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ በአሶሳ ከተማ የተጀመረው ውይይት የሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ አካል እንደሆነ ጠቁመው፤ ለሚቀጥሉት አራት ወራት እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡

ውይይቱ እስከ ቤተሰብ እንዲወርድ ይደረጋል ያሉት ዳይሬክተር ጀኔራሉ በውይይቱ ችግር ፈቺ መፍትሔዎች እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

የመተከል ጉዳይን አስመልክቶ በውይይት መድረኩ የተነሳው ቁጭት የተሞላበት አስተያየት ችግሩ በአጭሩ እንደሚፈታ አመላካች እንደሆነ ጠቁመው ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ ዛሬ የተጀመረው ማህበረሰብ አቀፍ የምክክር መድረክ እስከ ነገ እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃግብር መረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም