በጁንታው ላይ የተወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ሃገራዊ አንድነት ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና አለው–አቶ ርስቱ ይርዳው

713

ሀዋሳ ታህሳስ 12 /2013 (ኢዜአ) በከሃዲው የህወሓት ጁንታ ላይ የተወሰደው ህግ የማስከበር ርምጃ ሃገራዊ አንድነትንና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳለው የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ተግባራት አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ ለመምከር በሀዋሳ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ እንደተናገሩት ጁንታው በብሔር ብሔረሰቦች ስም ሀገራዊ አንድነት እንዳይኖር ሲሠራ ቆይቷል።

በዚህም በህዝብ ፍላጎት በመጣው ለውጥ ተገፍቶ ቦታውን መልቀቁን አውስተዋል፡፡

ጁንታው በህገወጥ መንገድ ባከማቸው ሀብትና በጥቅም ባደራጃቸው የጥፋት  ቡድኖች በመታገዝ ለውጡን ለማደናቀፍ  ሲጥር እንደነበርም አቶ ርስቱ ገልጸዋል።

ይባስ ብሎ የሃገር ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የተሰማራውን የመከላከያ ሠራዊት በማጥቃት በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ጭካኔ ማሳየቱን አስታውሰዋል፡፡

ይህን ክፉ ቡድን ለመደምሰስ መላው ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም በተወሰደ ህግ የማስከበር እርምጃ የተገኘው ስኬት ሃገራዊ አንድነት ለማምጣት እንደሚያስችል  አስታውቀዋል።

በቀጣይ ሃገራዊና አካባቢያዊ ሠላምና ፀጥታን በማጠናከር የተጀመሩ የመንግስት የልማት አቅጣጫዎች ውጤታማ በማድረግ ሃገሪቱ ያለመችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በሙሉ አቅም ርብርብ እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በመኸር ግብርናና በአረንጓዴ አሻራ ልማት እንዲሁም በእንስሳትና ዓሣ ሃብት የተከናወኑ የልማት ተግባራት መልካም ቢሆኑም ያለውን አቅም ለመጠቀም ቀሪ ተግባራት በመገምገም  አመራርና ህዝቡን በመቀናጀት መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በገጠርና ከተማ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመሰረተ ልማቶችና መስኖ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ጁንታው በጠነሰሰው  ክፉ ሴራ ላለፉት ሶስት ዓመታት ተከስቶ የነበረው የሠላም መደፍረስ ቡድኑ ላይ በተወሰደው ጠንካራ ህግ የማስከበር ርምጃ መስተካከሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የብልጽግና ፓርቲ የህዝቡን ፍላጎት በማዳመጥ በየደረጃው ከጸረ ሠላም ሃይሎች ጋር ያነበሩ ከ1 ሺህ 600 በላይ አመራሮች የማስጠንቀቂያ፣ ከቦታ ማንሳትና በህግ ተጠያቂ የማድረግ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።

በቦታቸውም በህዝብ አመኔታ ያተረፉ፣ የመሥራት ፍላጎትና አቅም ያላቸው ከ800 በላይ አዳዲስ አመራሮች በመመደብ የህዝብ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አመራሩ  የብልጽግናን ግብ በሁለንተናዊ ስኬት ለማጀብ መረባረብ እንዳለበት አመልክተው ፓርቲው ሁኔታዎችን በመገምገም የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በመድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የዞን አስተዳዳሪዎችና ሥራ አስፈጻሚዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡