በክልሉ የ3 ሺህ 163 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

75

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 12/2013 ( ኢዜአ) ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ 3 ሺህ 163 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ምንይሽር ለኢዜአ እንደገለጹት የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማቱ ግንባታቸው ባለፈው አመት ተጀምሮ በበጀት እጥረት ምክንያት ሳይጠናቀቁ የተዛወሩ ናቸው።

በግንባታ ላይ ያሉትን የእጅ ጉድጓድ፣ ምንጭ ማጎልበት፣ መካከለኛና ከፍተኛ ጥልቅ ጉድጓድ የውሃ ተቋማት ለማጠናቀቅ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ጠቅሰዋል።

ተቋማቱ በበጀት በዓመቱ መጨረሻ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ 698 ሺህ ሰዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።

የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት 66 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 69 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያሳድጉትም ጠቁመዋል።

በክልሉ  በተጠናቀቀው በጀት አመት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት በበቁ 6 ሺህ 533 የውሃ ተቋማት  ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም