በውጭ ሀገራት እየኖሩ የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከኢንተር ፖል ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል ይሰራል-የፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሀገራት እየኖሩ የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከኢንተር ፖል ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል ይሰራል-የፌደራል ፖሊስ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 11/2013 ( ኢዜአ) በውጭ ሀገራት እየኖሩ ከጁንታው ጋር ተባባሪ በመሆናቸው የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
በፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክትል ኮሚሽነር በዚህን ወቅት ጁንታው ከተሞችን ለቆ ከመሸሹ በፊት በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የነበሩ ወንጀለኞችን መሳሪያ አስታጥቆ በመልቀቅ በከተሞች አካባቢ ዝርፊያ እንዲፈጽሙ ማድረጉን ነው የገለጹት።
እነዚህ ወንጀለኞች የመንግስት ተቋማትን ንብረት ጭምር መዝረፋቸውን ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ህገ-ወጡ የህወሓት ጁንታ የክልሉ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዳያገኙ ለማድረግ በመንግስት ተቋማት ያሉ ሰነዶችንና ሰነድ የያዙ ኮምፒውተሮችን አቃጥሎ መሸሹንም ገልጸዋል።
ይህም ቡድኑ ከራሱ ስልጣን ውጭ ለህዝብ ምንም አይነት ደንታ የሌለው መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የክልሉ ነዋሪ ህዝባዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የገለጹት።
ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በህግ የሚፈለጉ ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።
በእስካሁኑ ሂደት በቁጥጥር ስር የዋሉና በቅርበት ክትትል እየተደረገባቸው ያሉ ተፈላጊዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አስፈላጊው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ መረጃው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ሁሉንም የጁንታው አባላትን ለመያዝ አሁንም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በውጭ ሀገራት እየኖሩ ከጁንታው ጋር የወንጀል ተባባሪ በመሆናቸው የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
የፌደራል ፖሊስ በክልሉ ትልልቅ ከተሞች ተልዕኮ ወስዶ ወደ ስራ መግባቱንም ነው ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ ያስታወቁት።
"በክልሉ መደበኛ የፖሊስ ሥራ ለማስጀመርም የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች መቀሌ ገብተዋል" ብለዋል።
መኮንኖቹ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከዚህ በፊት መመሪያን ብቻ አክብረው ሲሰሩ የነበሩ የክልሉ ፖሊስ አባላትን በህዝብ በማስተቸት መደበኛውን የፖሊስ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያደርጉ መሆኑንም አመልክተዋል።
በክልሉ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው የጦር መሳሪያዎችን እየመለሱ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይም ፍተሻዎችን በማካሄድ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የፌደራል ፖሊስ እያከናወነ ያለውን ተግባር በመደገፍ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለህብረተሰቡ ምስጋና አቅርበዋል።