ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ

ታህሳስ 11/2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሓምዶክ ፤ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ ፋርማጆ፤ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሬቤካ ንያዴግ ዲ ማቢዮር ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን በትዊተር ገፃቸው ይፋ አድርገዋል።

መሪዎቹ ጁቡቲ እየተካሄደ በሚገኘው 38ኛው አስቸኳይ የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከመሪዎቹ ጋር የተናጠል ውይይት ካካሄዱ በኋላ ከኬንያ፤ከሶማሊያ እና ጅቡቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር በጋራ መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ''ከመሪዎቹ ጋር በአካባቢያችን አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየታችን ደስ ብሎኛል'' ነው ያሉት በትዊተር ገጻቸው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ያካተተ የልኡካን ቡድን ወደ ስፍራው አቅንቷል።

ጉባኤው በአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም