የቺሊፕሬዝዳንት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ ፎቶ በመነሳታቸው ተቀጡ

112

ታህሳስ 11/2013 ( ኢዜአ) የቺሊው ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ፒኔራ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ (ሰልፊ) ፎቶ በመነሳታቸው 3 ሺህ 500 ዶላር ተቀጡ።

ከ18 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት ቺሊ በየቀኑ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን እየመዘገበች ባለችበት ሰዓት ፕሬዝዳንቱ ጭምብል ሳያደርጉ ፎቶ መነሳታቸው ዜጎችን አስቆጥቷል።

ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ፒኔራ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኘው የባህር ዳርቻ ነው ከአድናቂያቸው ጋር ፎቶ የተነሱት።

በኋላም ከወዳጆቻቸው እና ከሌሎች ቺሊያውያን ትችት በማስተናገዳቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጓቿ በቫይረሱ የተያዙባት ቺሊ በጣም ጥብቅ የኮሮና መከላከያ መመሪያ ከተገበሩ ሀገራት አንዷ ነች።

ቺሊ ወረርሺኙን ለመከላከል በተገበረችው መመሪያ ውስጥ ጭምብል ሳያደርጉ መንቀሳቀስ ከሌሎች ቅጣቶች ውጪ ለእስር ጭምር ይዳርጋል።

ቺሊ በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ ሀገራት በበሽታው የተያዙት እና ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ሞት ካስመዘገቡ አንዷ ነች።

የሀገሪቱ ዜጎችም መንግስት የቫይረሱን ስርጭት በሚገባ አልተከላከለም በሚል በተለያዩ ጊዜያት የተቃውሞ ሰልፎችን አካሂደዋል።

እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሃዛዊ መረጃ በቺሊ እስካሁን 581 ሺህ 135 በቫይረሱ ሲያዙ የ16 ሺህ 51 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

ምንጭ-ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም