በሐረር ከተማ "እኔም ለመከላከያ ሠራዊት እሮጣለው" በሚል የተዘጋጀ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄደ

73

ሐረር ታህሳስ 10 /2013 (ኢዜአ)  በሐረር ከተማ "እኔም ለመከላከያ ሠራዊት እሮጣለው" በሚል የተዘጋጀና ከ3ሺሕ በላይ ሰዎች የተሳተፉበት የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሄደ::

ውድድሩ ያዘጋጁት የምስራቅ ሐረርጌ ዞን እና የሐረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን በጋራ ነው።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ጁንታው ሀገሪቱንና  ህዝቡን ለማተራመስ  ያሰበው ሴራ በአጭር ጊዜ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ማክሸፍ ተችሏል።

በዚህም መደሰታቸውን ገልጸው ሠራዊቱ ያስመዘገበው ድል አንድ ያደረገውን የአካባቢውን ማህበረሰብ አብሮነቱነ ይበልጥ ለማጎልበት የሩጫ ውድድር መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር  አቶ ናስር ሁሴን በበኩላቸው፤ ጁንታው በመከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ጥቃትና ክህደት ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሩ የመከላከያ ሠራዊቱ በጥፋት ቡድን ላይ በወሰደው ህግ የማስከበር ስራና የተገኘውን አኩሪ ገድል ለመዘከር መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ መሰል የስፖርት ውድድሮች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ስፖርት  ኮሚሽነር ተወካይ አቶ ሳለህ አብዱልዋሲ "ውድድሩ ማህበረሰቡን በስፖርት የጀመረውን አንድነት በሌሎችም እንዲያጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል" ብለዋል።

በዕለቱ በወንዶች በተካሄደው ውድድር  ሳዳም አብዱለጢፍ ፣ሻሚ አብራሂም እና ሙሉጌታ ፈጠነ  ሶስቱም ከሐረሪ ክልል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመሆን አሸንፈዋል።

በሴቶች ደግሞ  አዚዛ ሙክታር  እና ሙኒሻ ሲራጅ  ከሐረሪ ክልል አንደኛ እና ሶስተኛ ፤ አሪፋ መሀመድ ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሁለተኛ ሁለተኛ ወጥታለች።

አሸናፊዎቹ የተዘጋጀላቸውን የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በውድድሩ የተሳተፉት ከሐረሪ ክልልና  ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የተውጣጡ ከ3ሺ በላይ   ስፖርተኞችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው።

መከላከያ ሠራዊቱ ጁንታውን ሥርዓት ለማሲያዝ ባካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ  ላስመዘገበው ውጤት  ለማመስገን በተዘጋጀው በዚሁ የውድድር ሥነ- ሥርዓት  ከፍተኛ  አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም