ያልተሳካው የጁንታው ተሟጋቾች ትርክት - ኢዜአ አማርኛ
ያልተሳካው የጁንታው ተሟጋቾች ትርክት
መንግስቱ ዘውዴ /ኢዜአ/
መቀሌ መሽጎ የነበረው የህወሃት ጁንታ ቡድን የሀገር ሉአላዊነትን በሚያስከብረው በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በድንገት ጥቃት በመሰንዘር ክህደት ፈጽሟል ። ድርጊቱ የተፈጸመው በትግራይ ልዩ ሃይልና ሚላሻ ሲሆን የጁንታው ቡድን ቀጥተኛ አመራር በመስጠት የተፈጸመ ነው።
የሀገርን ዳር ድንበር በማስከበርና ሉአላዊነቷ እንዳይደፈር በመጠበቅ ላይ በተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ከውጭ በመጣ ወራሪ ጠላት ሳይሆን ከውስጥ ከራሱ ወገን የተፈጸመው ይህ ጥቃት ኢትዮጵያውያንን ከማስቆጣቱም ባሻገር የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሲያነጋግር ቆይቷል ። ጥቃቱን ተከትሎ መንግስት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የፈጸሙትንና ያስፈጸሙትን አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ህግ የማስከበር እርምጃ ወስዷል ።
ይህንን ህግ የማስከበር ዘመቻ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅርበት ትኩረት ሰጥቶ ሲከታተለው ቆይቷል።
መንግስት ሲያካሄደው በነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻ የተለያዩ መረጃዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሰራጩ ሲሆን ብዙዎቹ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ነበሩ ። በተለይም አንዳንድ ታዋቂ ዲፕሎማቶች፣ ዓለም አቀፍ ተንታኞችና መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ገና ከጅምሩ ሲያሰራጯቸው የሰነበቱት መረጃዎች ከእውነታ የራቁ ፣ ሚዛናዊነት የሌላቸውና ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘቡ ነበሩ። ከሁሉ የሚገርመው የጁንታውን ቡድን የሚያሞጋግሱና የህግ የማስከበር ዘመቻውን የሚያጣጥሉ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ውስጥ መግባታቸው ነው።
ለዚህም ስራዬ ብለው የተዛባ መረጃ በየእለቱ በሰዓታት ልዩነት በቲውተር ገጻቸው ላይ በማስፈር እንዲሁም ትንታኔዎችን በመስጠት አሊያም “ተደራደሩ” የሚል ይዘት የያዘ መልእክት በማሰራጨት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ ምስል እንዲኖረው ጥረት አድርገዋል።
በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መስክ ሰፊ ልምድ ያካበቱት ኸርማን ኮህን መንግስት ህግ የማስከበር ዘመቻውን እንደጀመረ በቲውተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የመከላከያ ሠራዊት ልምድና ብቃት እንደሌለው በመጠቆም የህወሃትን ልምድ ያለው ጦር ማሸነፍ ከባድ ስለሚሆን ወደ ውጊያ ከመሄድ ይልቅ መወያየት ያስፈጋል ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኸርማን ኮህን በዲፕሎማሲ መስክ ከካበተ ልምዳቸው አኳያ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በዚህ መልክ ብቃት እንደሌለው መግለጻቸው ለትዝብት የዳረጋቸው መሆኑ እንጂ ሠራዊቱ ከሀገር አልፎ ለሌች አገራት ሰላም ማስከበር ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ያለ ስለመሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይመሰክራል።
እኚህ ዲፕሎማት በሌላ ጽሑፋቸው ላይ የፌዴራል መንግስቱ በህወሃት ላይ “የበቀል እርምጃ እየወሰደ ነው” ሲሉ አስፍረዋል።
ይህም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት እንጂ ከመንግስት ወገን ያለውን መረጃ በመውሰድ ሚዛናዊ መሆን ጠፍቷቸው አይደለም።
የጁንታው ቡድን ጥፋቶች በይፋ እየተነገረ አንድም ቀን ሳያወግዙ መቅረታቸው ከቡድኑ ጋር የከረመ ግንኙነት እንደነበራቸው ያሳብቅባቸዋል።
ኸርማን ኮህን በተለያዩ ጊዜያት በቲውተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሯቸው መረጃዎች የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ታስቦበትና ሆን ተብሎ የተሰራጨ እንጂ በቅን ልቦና የተመሰረተ ነው ለማለት አያስደፍርም። ጥቂቶቹን ለማሳያነት ያህል ብንመለከት፤-
“By initiating total armed warfare against Tigray, with the objective of preserving a unified Ethiopian state, PM Abiy is instead moving toward the disintegration of #Ethiopia through the mass killing of civilians, and the resultant unleashing of ethnic hatred nationwide’.
“Ethiopian civil war is about more than federal vs. regional power. When the TPLF controlled federal power for 29 years, the party built a major business monopolistic empire, especially truck transportation and construction, centered in Tigray.”
Nothing can justify the massacres of Tigrean civilians being reported in #Ethiopia. Moving towards reconciliation among all ethnic groups will require leadership from PM Abiy and Debretsion that they so far have not demonstrated. Foreign pressure for peace must be relentless.
Disappointed that #Ethiopia PM – and Nobel Peace Prize recipient – Abiy has chosen to go to war against Tigray instead of choosing dialogue to write a new constitution that will allow maximum self-determination for all the ethnic nations in an unprecedented true federal system.
ከዲፕሎማቶቹ በተጨማሪ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተንታኞችም ከላይ በተገለጸበት መልኩ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ጥረት አድርገዋል።
ማርቲን ፕላውት መሰረቱን እንግሊዝ በማድረግ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ትንታኔዎችን የሚሰጥ እንዲሁም institute of common wealth studies ተመራማሪ ነው። በዓለማችን ትልቁ መገናኛ ብዙሃን በሆነው ቢቢሲ ኤዲተር በመሆን በጋዜጠኝነት የቆየ ይሁን እንጂ የጋዜጠኝነትን መርህ ያልተከተሉ ሚዛናዊነት የጎደላቸው በርካታ ዘገባዎችን አሰራጭቷል።
ማርቲን ፕላውት መንግስት ህግን ለማስከበር የወሰደው እርምጃ በየእለቱ በትዊተር ገጹ ላይ ጉዳዩ ቀጠናዊ ለማስመሰል ጥረት አድርጓል። በሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት እንደተቀሰቀሰ በማስመሰል በተደጋጋሚ ጽፏል።
የህወሃት ቡድን አስመራ ላይ ያደረሰው የሮኬት ጥቃት አሜሪካና ሌሎች የዓለም አገራት ሲያወግዙ ማርቲን ፕላውት ግን የህወሃት ጁንታ ቡድንን ደግፏል። ኤርትራ ከዚህ በፊት ትግራይ ላይ ጥቃት ማድረሷን ዘንግተውት ነው? ሲል ሞግቷል።
ማርቲን ፕላውት በአልጀዚራ፣ ቢቢሲ በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ላይ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ የሰብአዊ ቀውስ እንዲፈጠር እንዳደረገ በተደጋጋሚ ተናግሯል። በሀገር መከላከያ ላይ ስለደረሰው ጥቃት ግን አንድም ቦታ ላይ ሲጠቅስ አልታየም።
ሀገሪቱ ወደ ከፋ የእርስ በርስ ጦርነት እንደምትገባ፣ ይህም ለአፍሪካ ቀንድ እጅግ ፈታኝ እንደሚያደርገው ሲናገር ቆይቷል። ምኞቱና ህልሙም ይህ ነበር፤ አልተሳካለትም እንጂ። ፕላውት እንደጋዜጠኛ በሁለቱም በኩል ያሉትን እውነታዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብ ነበረበት። እስካሁንም ሚዛናዊነት የጎደለው የአንድ ወገን መረጃ ማሰራጨቱን እንደቀጠለ ነው።
ረሺድ አብዲ በትውልድ ሶማሌያዊ ሆኖ የኬንያ ዜግነት ያለው ሲሆን “International Crisis Group” በሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ተንታኝ ነበር። በአሁኑ ወቅት በግሉ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ በመሆን እየሰራ ይገኛል። ረሺድ አብዲ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በማጠልሸት ይታወቃል። ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሌያ በጋራ መስራት በጀመሩበት ወቅት የሶስቱ ሀገራት ጥምረት ቀጠናውን ወደ ጦትነትና አላስፈላጊ ብጥብጥ እንደሚወስድ ትንታኔዎችን በመጻፍ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲያሰራጭ ነበር። መንግስት የወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ አስመልክቶ ሀገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊወስዳት እንደሚችል ጽፏል።
ከማርቲን ፕላውት ሃሳብ ጋር የሚመሳሰል ይዘት ያለው በተለይም “የአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ የሆነ ችግር ውስጥ ሊገባ ስለሚችል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ መግባት አለበት፣ ድርድር እንዲጀመር ጫና መፍጠር ይኖርበታል” በሚል በተደጋጋሚ ጽፏል።
ፕሮፌሰር ኬ ጄ ትሮንቮል የህወሃት ጁንታ ቡድን በትግራይ ክልል ህገ ወጥ ምርጫ ለማካሄድ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በመቀሌ ዩኒቨርሲቱ ተመራማሪነት ስም የኦን ላይን ቪዛ በመውሰድ ያለ ፌዴራል መንግስት እውቅና ራሱን ብቸኛ የዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢ ያደረገ ሰው ነው። ትሮንቮል የኖርዌይ ዜጋ ሲሆን በሰብአዊ መብት፣ በሰላምና ግጭት አፈታት ዙሪያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በርካታ መጽሐፎችን ጽፏል። ከእነዚህ መካከል “the Ethiopian Red terror trails , brothers at war, making sense of the Eritrean-Ethiopian war, Ethiopia; a new start, war and the politics of identity in Ethiopia” የሚሉት ይገኝበታል።
በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚሰጣቸው ማብራሪያዎች ሚዛናዊነት የጎደላቸው ናቸው። በተለይ በቲውተር ገጹ ላይ በሚያሰፍራቸው ሃሳቦች መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደፈጸመ ለማስመሰል ይሞክራል። በክልሉ የሰብአዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ አካል ሊጣራ ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ይገልጻል። የፌዴራል መንግስት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ አድርጓል ከሚለው በተጨማሪ የኮሙዩኒኬሽን አውታሮችን አጥፍቷል በማለት በተደጋጋሚ ገልጿል።
ትሮንቮል ከራሺድ አብዲ ጋር በቲውተር ገጻቸው ላይ በመቀባበል በሚያሰፍሩት ሃሳብ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳሳት እየሰሩ ይገኛል። በተደጋጋሚ በሚያሰራጨቸው መረጃዎች ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት በማምራት ላይ እንደምትገኝ፣ ንፁሃን ዜጎች እየተጎዱ ስለመሆኑ፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ፣ በመንግስት ላይ ማእቀብ በመጣል ጫና እንዲያሳድር ይወተውታሉ።
ትሮንቮል እና ራሺድ አብዲ የኤርትራ ሰራዊት ትግራይ ውስጥ መግባቱንና ታሪካዊ ቅርሶችን እየዘረፉ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ላይ እንደሚከተለው አስፍረዋል። ይህ መረጃ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በተለይም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ትኩረት የሚያደርጉ አገራትን ለማነሳሳት ስለመሆኑ መረጃው ይመሰክራል።
በማንኛውም ሀገር ወቅታዊ የሆኑ ሰው ሰራሽ አሊያም ተፈጥሯአዊ ክስተቶች ያጋጥማሉ። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ የክስተቱ አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ገጽታ በትክክል ተገንዝቦ አስፈላጊውን ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ ትክክለኛና ተአማኒነት ያለው ወቅታዊ መረጃ ወሳኝ ነው። የመገናኛ ብዙሃን፣ ዓለም አቀፍ ተንታኞች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ከሙያቸው አስገዳጅነት አንፃር የሚሰጧቸው መረጃዎች በአብዛኛው ትክክለኛ ተደርገው ይወሰዳሉ። ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባላቸው ተደራሽነትና ታዋቂነት የሚያሳድሩት ተጽእኖም ቀላል አይደለም።
በሀገራችን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በየትኛውም ሀገር ተቀባይነት ያለው አይደለም። መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉአላዊነት የሚጠብቅ ለህዝቡ ደህንነት የቆመ በምግባረ መልካምነት የታነጸ ሃይል ነው።
በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም ማለት የሀገር ህልውናን አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። ይህ እውነታ ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ ለተንታኞችና ዲፕሎማቶች ቀርቶ ለማንም ሰው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቃቀሱና ሌሎችም መሰሎቻቸው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን ማሳየት ተስኗቸው አይናቸውን በጨው አጥበው ሙግት ተያይዘዋል።
በአገር ጉዳይ ገብተው ለመተንተን ሞክረዋል። በአንፃሩ አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩ የውስጥ መሆኑን ተገንዝቦ መንግስት የያዘውን አቅጣጫ ደግፏል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባደረገው ገድል በከሀዲው ሃይል የደረሰበትን ጥቃት ከመከላከል አልፎ ማንም ባልገመተው ፍጥነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጁንታውን ከስሩ ነቅሎ ጥሎታል። የትግራይ ክልል ህዝብም ከጁንታው የአገዛዝ ቀንበር ተላቅቆ አዲስ ምእራፍ ጀምሯል። አንዳንድ ዲፕሎማቶችና ተንታኞች እንደተመኙት ሀገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት አልገባችም። የቀጠናው መልካም ግንኙነትም እንደቀጠለ ይገኛል።