ሀገራዊ የሙያ ብቃት ያለው ፖሊስ ለማፍራት የሚያስችል የስልጠና ሰነድ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ 7/2013 (ኢዜአ) ሀገራዊ የሙያ ብቃት ያለው የፖሊስ ሰራዊት ለማፍራት የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮምሽነርና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት መስፍን አበበ ገለጹ።

የፖሊስ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ደረጃ ምዘና ለመስጠት የተዘጋጀ ሰነድ ዙሪያ ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ምክክር ተጀምሯል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በምክክሩ ላይ እንደተናገሩት ቀደም ሲል በሃገሪቱ የነበረው የፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ደረጃና ምዘና አልነበረውም።

በዚህ ምክንያትም ፖሊሳዊ ሙያ እንደ ማንኛውም የሙያ ዘርፍ ደረጃ ወጥቶለት እየተሰራ እንዳልነበረም አስረድተዋል። 

ሰነዱ በሀገሪቱ ደረጃ በፖሊስ ሙያ ላይ ያሉት ተመሳሳይ የሙያ ብቃት፤ ክህሎት እውቀት ያለውና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑንም ገልጸዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።

“በዚህ ሰነድ ከዲግሪ በታች ያሉት ፕሮግራሞች የትምህርትና ስልጠናዎች ደረጃ በማውጣት እውቅና እያገኙ ይሄዳሉም” ብለዋል።

የፖሊስ ሰራዊቱ የሙያ ብቃት ፈተና በመውሰድ ብቁና ተወዳዳሪ አንደሚሆን ጠቅሰው፤ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወን ነውም ብለዋል::

“በሰነዱ ትግበራ በአገሪቱ ያሉት የፖሊስ ሰራዊት አባላት ተመሳሳይ ሙያ፤ እውቀት፤ ክህሎት፤ ክፍያና ጥቅማጥቅም እንዲያገኙ ያስችላል” ብለዋል::

የኦሮሚያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ኢታና እንዳስታወቁት ከአሁን ቀደም በሀገሪቱ የፖሊስ ሙያ ደረጃና ምዘና ባለመኖሩ ከፍተኛ ችግር ነበረበት።

እንደ ኦሮሚያ ክልል ለጥናት የሰነዱ ሀሳብ ለማመንጨት መሞከራቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጥናቱ በፖሊስ ሙያ ላይ እንደ ሀገር ያለውን ችግር ሊፈታ የሚያስችል ነው ብሎ በማመኑ ለመላው ሀገሪቱ እንዲሆን ተደርጓል ነው ያሉት።

በነበረው የሀገሪቱ የፖሊስ ስልጠና ፕሮግራም ፖሊስ ተመርቆ ሲወጣ ከፖሊስ ተቋማት ውጭ ሌሎች ተቋማት ላይ ተቀባይነት እንዳልነበረውም ተናግረዋል።

ስለሆነም የፖሊስ ሰራዊቱ ወደ ተቋሙ ሲመጣ ጊዜያዊ ችግሩን አይቶ እንጂ ፈልጎ ባለመሆኑ ሌሎች ሙያዎችን በመማር ክፍተኛ ፍልሰት መኖሩንም አስረድተዋል።

የተዘጋጀው በጥናት ላይ የተመሰረተው ሰነድ በፍኖተ ካርታ የታቀፈ በመሆኑ "የዘመነና ሀገራችን የምትፈልገውን አገልግልት ለመስጠትና አገልጋዩም ተጠቃሚ የሚሆንበት ነው” ብለዋል።

በአዲሱ ሰነድ እንደተቀመጠው ሰልጣኞች 5ኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ዲግሪያቸውን መያዝና በአገሪቷ በየትኛውም ሙያ ላይ መወዳደር እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል።

በዋናነት በኦሮሚያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አቅራቢነት በተዘጋጀው የጥናት ሰነድ መሰረት የፖሊስ ሙያ ስልጠና እንደማንኛውም የሙያ መስክ ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ደረጃ ጀምሮ እስከ ዲግሪ ድረስ የሚያድግና ከሌሎች ሙያ ዘርፎች እኩል ተወዳዳሪ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም