የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አዋጅን አፀደቀ

105
አዲስ አበባ  ሀምሌ 13/2010 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በቀረበለት ረቂቅ የምህረት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል። አዋጁ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት እንደሚያግዝ የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል። የምህርት አዋጁ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተወረሱ ንብረቶችንና ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አያካትትም ተብሏል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እንደገለጹት፤ የምህረት አዋጁ ዓላማ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ የተሳተፉ ሰዎችን የወንጀል ተጠያቂነት በመሰረዝ ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው በአገር ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ማድረግ ነው። የምህረት አዋጅ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት እና በአገሪቱ ወንጀል ህግ እውቅና የተሰጠው መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው የአዋጁ አፈፃፀም ከመደበኛ ፍርድ ቤት በተጨማሪ ወታደራዊ ፍርድ ቤትንም ያካትታል። ከወታደራዊ ተቋማት የኮበለሉ ወንጀለኞችም የምህረት አዋጁ አካላት እንዲሆኑ ተደርጓል። ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ምህረት የተደረገለት ግለሰብ ሪፖርት ለማድረግ ይሰጠው የነበረው የሁለት ወር ጊዜ በፀደቀው አዋጅ ላይ እስከ ስድስት ወር እንዲራዘም ሆኗል። በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 7/4 "ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከሚለው ቀጥሎ ወይም ለክልል ፍትህ ቢሮዎች" የሚል ሐረግ ታክሎበታል። በዚሁ መሰረት የምህረት አዋጁ በሽብርተኝነት፣ ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት፣ በአገር ላይ ጉዳት ያደረሱ ተብለው የተከሰሱትን የሚያካትት  ሲሆን በአስገድዶ መድፈር፣ በዘር ማጥፋት፣ በሰው ግድያና በሙስና ወንጀል እንደዚሁም የኢሰብዓዊ ድርጊት ወንጀለኞችን አንደማይመለከት ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል። በምህረት አዋጁ የወጣው በተለያዩ የወንጀል አይነቶች ተሳትፈው የነበሩና በህግ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው ተመልሰው የመንግስትን ህግና ስርዓት አክብረው ለመንቀሳቀስ ግዴታ ለሚገቡ ወይም ሊገቡ ይችላሉ ተብለው ለሚታሰቡ ግለሰቦች ነው። "አዋጁ መንግስት ክሳቸው በምርመራ ሂደት ላይ የሚገኙ፣ የተከሰሱ፣ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ፣ ገና ያልተያዙ ሰዎች ወይም ቡድኖች ያለፈው ጥፋታቸው ሙሉ በሙሉ እንዳልተሰራ የሚቆጥርበት ነው" ሲሉ አቶ ጴጥሮስ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል። የምህረት አዋጁ ግለሰቦቹ ወደ ህብረተሰቡ በመግባት በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እድል የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል። በምህረት አዋጁ በተዘረዘሩ የወንጀል አይነቶች ውስጥ የተሳተፉ ወይም የተጠረጠሩ በአገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ሰዎች ወይም ቡድኖች በፖለቲካ አመለካከት ልዩነትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች በዜጎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የእርስ በእርስ ጥላቻና አለመተማመን ለማስወገድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። እንዲሁም ይቅር በመባባል መንፈስ ወደ ህብረተሰቡ ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ ለመቀጠልና ለአገራቸው ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋዕኦ እንዲያበረክቱ እድል ይሰጣቸዋል። እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያግዝ  በመሆኑ ምክር ቤቱ በአንድ ድምጸ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም