አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ሃዋሳ ከተማ ተለያዩ

99
አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2010 ለአራት አመታት ከሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ጋር የቆዩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የገቡት ውል ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በመጠናቀቁ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል። ክለቡ ውሉን እንዲታደስ ጥያቄ ቢያቀርብላቸውም አሰልጣኝ ውበቱ መቀጠል ባለመፈለጋቸው ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል። ከሌሎች ክለቦች ጋር ድርድር የጀመሩት አሰልጣኙ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቀጣይ ማረፊያቸውን እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል። አሰልጣኝ ውበቱ ከክለቡ ጋር ሆነው የመጨረሻ ጨዋታ ትናንት በይርጋለም ስታዲየም በኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረጉ ሲሆን በውጤቱም ሲዳማ ቡና ሃዋሳ ከተማን በመለያ ምት 5 ለ 4  በሆነ ውጤት አሸንፏል። በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሃዋሳ ከተማ 36 ነጥብ በመሰብሰብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዚህ በፊት ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ ቡናና አዳማ ከተማን አሰልጥነዋል። አሰልጣኙ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በመሆን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በ2003 ዓ ም የውድድር ዘመን አንስተዋል። በተጨማሪም በሱዳኑ አህሊ ሺንዴ ክለብም በአሰልጣኝነት ሰርተዋል። አሰልጣኝ ውበቱ ኳስን ይዞ በመጫወት ፍልስፍናቸውና ለወጣት ተጫዋቾች በሚሰጡት የመጫወት እድል ከስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አድናቆት የሚቸራቸው ናቸው። የመቀሌ ከተማው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌና የፋሲል ከተማው መሳይ ተፈሪ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ውላቸው በመጠናቀቁ ምክንያት ከክለቦቻቸው ጋር መለያየታቸው የሚታወስ ነው።                              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም