በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች በተደራጀና በታቀደ መንገድ በውክልና የሚፈጸሙ ነበሩ... ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች በተደራጀና በታቀደ መንገድ በውክልና የሚፈጸሙ ነበሩ... ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉ በተደራጀና በታቀደ መንገድ በውክልና የሚፈጸሙ እንደነበሩ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።
ለግጭቶች ሁሉ መንሰኤ የነበረው የሕወሃት ቡድን አባላትን በቅርቡ ለሕግ ለማቅረብ የመከላከየ ሰራዊት ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑንም የመከላከያ ሚኒስትሩ ቀነዓ ያደታ ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልና የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታን ማብራሪያ ጠይቀዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን፤ በየቦታው የሚነሱ ግጭቶችንና ለምን ማስቆም እንዳልተቻለ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በኢትዮጵያ ካለፉት 2 ዓመታት ወዲህ በየቦታው የሚያጋጥሙ ግጭቶች መንስኤን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ግጭቶች፣ ፋይናንስ ሲደረጉና ዕቅድ ወጥቶላቸው ተፈጻሚ የነበሩ ናቸው ብለዋል።
ይህም ከፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ሆነው የሚመሩት፣ በየአካባቢው ወጣቶችን በማደራጀት በውክልና ጦርነት የሚደረጉ እንደነበሩ አንስተዋል።በኢትዮጵያ በማንኛውም አካባቢ የሚነሱ ግጭቶች ዋናው ምንጭ ከአንድ ቡድን መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የሰዎች ዝውውር፣ የገንዝብ፣ የጦር መሳሪያና ኮንትሮባንድ ወንጀሎች በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ትስስር የነበራቸው እንደነበሩም እንዲሁ።የፀጥታ አካላት መዋቅራዊ ችግር ያለበት በመሆኑ በፖሊስና በደህንነት ተቋማት አመራሮች የሚሳተፉበት ስለነበር ከለውጥ ማግስት ተቋማዊ ማሻሻያ ያስፈልግ እንደነበርም አንስተዋል።
የፖሊስ ተቋማት ከሃይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ ከመንግስት ባህሪ ጋር የተጣመረ ሆኖ ዘልቆ በመጨረሻ እስከ ፓርቲ ሰነድ ላይ መወያያት የደረሰ እንደነበር፣ የደህንነት ተቋሙም መጠየቅ የማይችሉ የጥቂት ሰዎች ተቋም እንደበረ ከለውጥ በኋላም የፈረሰ ተቋም እንደነበር ገልጸዋል።
የፖሊስና የደህንነት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የጸጥታ ተቋማትን ከአገርና ከህዝብ ጋር የቆሙ እንዲሆኑ በተቀናጀ ሴራ ውስጥም ቢሆን ሲሰራ መቆየቱን በዚህም ትልቅ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።
በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችን በሙሉ ማስቆም ያልተቻለውም ‘ከበሬው ሌባ ጋር የጠፋን በሬ የመፈለግ ያህል ከባድ’ በመሆኑ ነበር ብለዋል።ይህም እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ከባድ እንደነበረ ገልጸዋል።
ሌሎች ሊፈጸሙ የነበሩ ከባድ የሽብር ወንጀሎች ማክሸፍ መቻሉን ገልጸው፣ በግጭቱ ሳቢያ በየቦታው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ዜጎችንም የመርዳትና የማቋቋም ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የምከር ቤቱ አባለትም በወቅታዊ የህግ ማስከበር ዘመቻና የህወሃትን ህገ ወጥ ቡድን አባላትን ለህግ አቅርቦ ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር ስለተከናወኑ ስራዎች ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በአገር መከላከያ ሰራዊት ወቅታዊ የሕግ ማስከበር ጉዳዮች ላይ በሰጡት ምላሽ የግጭቶች ሁሉ ምንጭ የነበረው የህወሃት ቡድን አሁን ላይ መፍረሱን ገልጸዋል።
ሰራዊቱ የጁንታውን ቡድን አባላት አድኖ ለሕግ ለማቅረብ ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑንም ተናገረዋል።