የማዕድን ማምረትና ምርምር ፈቃድ ተሰጥቷቸው የነበሩ 63 ተቋማት ፈቃዳቸው ተሰረዘ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ማምረትና ምርምር ፈቃድ ተሰጥቷቸው የነበሩ 63 ተቋማት ፈቃዳቸው ተሰረዘ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6/2013 ( ኢዜአ) የማዕድን ማምረትና ምርምር ፈቃድ ተሰጥቷቸው የነበሩ 63 ተቋማትን ፈቃድ መሰረዙን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ባለፉት አምስት ወራት ከዘርፉ 302 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በሰጡት መግለጫ የማዕድን ዘርፍ ከግብርና ቀጥሎ አገሪቷ ያላት ትልቅ ሀብት ቢሆንም በአግባቡ ባለመመራቱ ውጤታማ እንዳልነበረ ገልጸዋል።
በዘርፉ የውጭ ገቢ ምርቶችን መተካትና ወርቅና መሰል ማዕድናትን ወደ ውጭ በመላክ ማዕድን የኢኮኖሚው ምሰሶ ሆኖ እንዲቀጥል ላለፉት ወራት በትኩረት ሲሰራ መቆቱን አውስተዋል።
ለዘርፉ መሻሻል ኮሚቴ በማዋቀር ላለፉት አራት ወራት ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ፈቃድ ወስደው በዘርፉ በተሰማሩ ከ200 በላይ ኩባንያዎች ላይ ግምገማ መደረጉን ገልጸዋል።
በርካቶቹ አስተዳደራዊ ችግሮች፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የብድር አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮች እንዳሉባቸው መለየቱን ገልጸው፣ ችግራቸውን ለመፍታት በመንግስት በኩል ሥራዎች መሰራታቸውን አክለዋል።
በመንግስት ድጋፍ ተደርጎላቸው ሊሻሻሉ እንደማይችሉ የተገመገሙ 63 ከትንሽ እስከ ትልቅ ኩባንያዎች ላይ ፈቃዳቸውን የመሰረዝ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።
ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው 63 ኩባንያዎች መካከል 38 በማዕድን ማምረት፣ 25 ደግሞ በማዕድን ምርምር ላይ የተሰማሩ ናቸው።
ፈቃዳቸው የተሰረዘው በአፈጻጸም ድክመት፣ የሕዝብና የመንግስት ሃብት በማባከን፣ በወቅቱ ፈቃዳቸውን ባለማሳደስ፣ ከአቅም በታች በማምረትና የሮያሊቲ ክፍያ ባለመፈፀማቸው መሆኑን ሚኒስትሩ ዘርዝረዋል።
ሚኒስትሩ "የማዕድን ቦታዎቹ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡና የአገርና የሕዝብ ሀብቶች በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል" ብለዋል።
በማዕድን ኢንቨስትመንት መሳተፍ የሚሹ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስለሚገኙ በማዕድን ሀብቶች የተደራጀ መረጃ የሚያገኙበት የካዳስተር ፖርታል ስርዓት መዘጋጀቱንም ይፋ አድርገዋል።
በሕግ ማዕቀፍ ጉዳዮች ማሻሻያዎች መደረጋቸውን፤ ለአብነትም ፌዴራልና ክልሎች በራሳቸው ፈቃድ የሚሰጡበትና ተናበው የሚሰሩበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።
በዚህ አሰራር የቢሮክራሲን ችግር የሚቀርፍ የካዳስተር ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ለማዋል 80 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት አምስት ወራት 302 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከዘርፉ መገኘቱ በመግለጫው ተመላክቷል።
ከ4 ሺህ 83 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለውጭ ገበያ ቀርቦ 299 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ሲገኝ፤ ከጌጣጌጥ ማዕድናት ደግሞ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።
የኮንትሮባንድ ንግድን መቆጣጠር በመቻሉ የማዕድን ምርት ገቢ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በአንጻሩ ወርቅ ከሚወጣባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ትግራይ ክልል ላለፉት ሁለት ወራት ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳልገባና ሽሬ ላይ 470 ኪሎ ግራም በህወሓት ጁንታ መዘረፉን አያይዘው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከየትኛውም አገር በተሻለ በባህላዊ መንገድ ወርቅ አምራች መሆኗን የገለጹት ኢንጂነር ታከለ፤ "ዘርፉ በአግባቡ ከተመራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ወርቅ አምራች የማትሆንበት ምክንያት የለም" ብለዋል።
በትላልቅ ኩባንያዎች በኩል የሚመረተው የወርቅ መጠን አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ እንደ ግብርናው ትኩረት ቢተቸረውና ጥራት ያላቸው ጥቂት ኩባንያዎች በወርቅ ማምረት ቢሰማሩ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አረጋግጠዋል።