ሠራዊቱ በአገሩ የማይደራደር እንደ አባቶቹም ጀግንነትን የሚፈጽም የድል ሠራዊት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

74

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአገሩ የማይደራደር፤ እንደቀደሙት አባቶቹ ጀግንነት በመፈፀም ታሪኩን በደማቅ ቀለም ያስመዘገበ ድንቅ የሕዝብ ልጅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሰከሩ፡፡

ሠራዊቱ በህወሓት ጁንታ ላይ የተቀዳጀውን ድል ሕገወጡን ቡድን ለሕግ በማቅረብ ጀግንነቱን ዳግም እንዲያስመሰክር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመቀሌ የሕግ ማስከበር ሂደቱን ከመሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር ሲወያዩ ሠራዊቱ በአገሩ የማይደራደር እንደ አባቶቹ ጀግንነትን የሚፈጽም የድል ሠራዊት ነው ብለዋል።

የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በኩራት በማጠናቀቁም 'ክብር ይገባዋል' ነው ያሉት፡፡

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስጠብቅና ለክብሯ የቆመ የአገር መከላከያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሕግ ማስከበርው ዘመቻው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ በአጭር ጊዜ የተጠናቀቀና ለውጤት ያበቃ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ታላቅ አገር ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት ሠራዊቱም አገር የመታደግ ሃላፊነት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሠራዊቱ ከተሰጠው ተልዕኮ በተጨማሪ በትግራይ ክልል የፈረሱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ሠራዊቱ የተሰጠውን የመጀመሪያ ተልዕኮ በብቃት ፈጽሟል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕግ ማስከበር ሂደት ያስመዘገበውን ድል ወንጀለኞችን ይዞ ለሕግ በማቅረብ ሊደግመው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የትግራይ ክልል ሕዝብም ወንጀለኞች ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም