የሕወሃት ቡድን በክፋት ተመስርቶ፣ በክፋት ኖሮ፣ በክፋት የጠፋ ነው -ደራሲና የታሪክ ጸሃፊው ገስጥ ተጫኔ

154

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3/2013 ( ኢዜአ) "የሕወሃት የጥፋት ቡድን በክፋት ተመስርቶ፣ በክፋት ኖሮ፣ በክፋት የጠፋ ነው" ሲሉ ደራሲና የታሪክ ጸሃፊው ገስጥ ተጫኔ ገለጹ።

የጥፋት ቡድኑ በዘር ማጥፋትና ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በጦር ወንጀልና በአገር ክህደት ወንጀሎች ሊጠየቅ ይገባዋልም ብለዋል።

‘ዘነበ ፈለቀ’ በሚል የብዕር ስም የሚታወቁት ደራሲና የታሪክ ጸሃፊ ገስጥ ተጫኔ የቀድሞ ሰራዊት የአየር ወለድ አባል ነበሩ።

እርሳቸው በቀድሞው ጦር ሰራዊት ታሪክን ጨምሮ እስካሁን ከ10 በላይ መጻህፍትን ለአንባቢያን አበርክተዋል።

ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ድሕረ ፋቪስት ጣሊያን ወረራ የተቋቋመው የጦር ሰራዊት በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ መንግሥታት ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሞከሩ ወራሪዎችን የመከተ ከሆለታ እስከ ሐረር ጦር ትምህርት ቤቶች የሰለጠነ ብቃት ያለው ሰራዊት እንደነበር ይናገራሉ።

ከተገንጣዮች ጋር  ከ30 ዓመታት በመታገል ከራሱ በላይ አገሩን በማስቀደም ዋጋ የከፈለ ሰራዊት እንደሆነም ይናገራሉ።

‘መንግሥታት ይለዋወጣሉ፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት ግን ይቀጥላል’ የሚሉት ደራሲው፣ ወያኔ አገሪቷን ሲቆጣጠር ግን በተቃራኒው ለግማሽ ምዕተ ዓመት የተገነባ ሰራዊት እንደበተነ ይገልጻሉ።

ወያኔ ከመሰረቱ ኢትዮጵያዊ አስተሳስብ እንዳልነበረው ገልጸው፤ ቡድኑ ገና ጫካ እያለም የማረካቸውን የሰራዊት አባላት በመርዝ እንደገደላቸውም ይናገራሉ።

'እናም የህወሃት ቡድን በክፋት ተመስርቶ፣ በክፋት ኖሮ፣ በክፋት የጠፋ ነው' ይላሉ።

ከሰራዊቱ ባሻገርም በታሪክ፣ በባህልና በሥነ ልቦና የጋራ መስተጋብር ያለውን ሕዝብ ለአገዛዙ እንዲመቸው ብቻ ዘር ለይቶ እርስ በርስ በማጋጨት ወንጀል መስራቱን ገልጸዋል።

ጁንታው በቀድሞው ጦር እንዲሁም በአሁኑ የሰሜን ዕዝ ሰራዊት ላይ በዓለም የጦር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ከፍተኛ የጦር ወንጀል እንደሆነ ተመራማሪው ተናግረዋል።

ቡድኑ በንጹሃን ላይ ዘር ለይቶ ላደረሰው ጥፋት በዘር ማጥፋት ወንጀልና ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲጠየቅ፣ በጦር ሰራዊቱ ላይ ለፈጸመው ግፍና በደልም በጦር ወንጀል ሊከሰስ ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል የአገርን ክብር ለመጠበቅና ሉዓላዊነት ለማስከበር የጦር ሰራዊት አለማሰናዳት ወይም ዝግጁ አለማድረግ ወንጀል እንደሆነ ገልጸው፤ ወያኔ ግን የቀድሞው እንዲበተንና በአዲስ የተቋቋመው እንዳይጠናከር አድርጓል ብለዋል።

ከሃዲው ቡድን አንድም ጊዜ ኢትዮጵያን አስቦ እንደማያውቅ ይልቁንም የዚያድ ባሬ ሶማሊያ ጦር በግፍ ኢትዮጵያን በወረረች ወቅት ለጠላት ድጋፍ ያደረገና በጠላት አገር ፓስፖርትም ሲንቀሳቀስ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም የሕወሃት ቡድን ከዱሮ እስከ ዘንድሮ ኢትዮጵያን የከዳ በመሆኑ በከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል ሊጠየቅ ይገባል ነው ያሉት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም