ተማሪዋ ጨቅላ ልጇን ታቅፋ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየወሰደች ነው

64

ድሬዳዋ/ኢዜአ/፣ ታህሳስ 2 /2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ከትላንት በስቲያ ህጻን ልጇን የተገላገለች ተማሪ የስምንተኛ ከፍል ክልላዊ ፈተና እየወሰደች ነው።

ወላዷን ጨምሮ በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ ለሚገኙ ከ7 ሺህ በላይ ተማሪዎች የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ትናንት መሰጠት መጀመሩን የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የሀሎ በሶ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ደሰቱ አደም ሙሳ ከትላንት በስቲያ የመጀመሪያ ሴት ልጅዋን መገላገሏን ለኢዜአ ተናግራለች።

ትምህርቱን የለፋችበት በመሆኑና ለትምህርቱም ባላት ጉጉት የተነሳ ጨቅላ ልጇን ታቅፋ ፈተናውን እየወሰደች መሆኗን ገልጻለች፡፡

"አንድ ዓመት ማባከን አያስፈልግም ፤ ሴት ልጅ የማትወጣው ፈተና የለም፤ ፈተናውም ቀድሜ ስለተዘጋጀሁበት ጥሩ ነው" ስትልም ተማሪ ደሰቱ ተናግራለች፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ-መምህር አቶ ብሩክ አሰፋ በበኩላቸው፤ ተማሪ ደሰቱ ለአራሷና ለጨቅላው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ፈተናውን ተረጋግታ እየተፈነች መሆኗን ገልጸዋል።

የከዚራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ትዕግስት ክብሩ እንደተናገረችው፤ ፈተናውን በተዘጋጀችበት ልክ ተረጋግታ እየተፈተነች ትገኛለች፡፡

በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት መምህራን ባደረጉላቸው የማካካሻ ትምህርትና ቤተሰቦቹ ባደረጉላት ድጋፍ ለፈተናው ዝግጁ ሆና እየወሰደች እንደምትገኝ የገለጸችው ደግሞ የቤተ ናታል ትምህርት ቤት ተማሪ ዮሃና ሀብታሙ ናት።

ተማሪ ዮሃና "እስከ አሁን የፈተናው አወጣጥ ጥሩ ነው፤ ጎበዙንም መካከለኛ ተማሪውንም ያማከለ ነው ብላለች።

የድሬዳዋ አሰተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሃመድ እንደተናገሩት፤ ክልላዊ ፈተናውን እየወሰዱ የሚገኙት ተማሪዎች በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርታቸውን በክለሳ የወሰዱ ተማሪዎች ናቸው፡፡

በፈተናው ላይ ከግልና መንግስት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 7 ሺህ 113 ተማሪዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ክልላዊ ፈተናው ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዙ የጥንቃቄ መስፈርት በማሟላት እየተሰጠ እንደሚገኝም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ትናንት የተጀመረው ክልል አቀፍ ፈተናው እስከ ቅዳሜ ድረስ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም